የማህፀን ጫፍ ካንሠር መከላከያ ክትባት በተለያዩ ክልሎች ከ9 እስከ 14 ዓመት ለሆናቸው ታዳጊ ሴቶች ዛሬ መሰጠት ጀምሯል።
በዘመቻ መልክ እየተሰጠ ያለው ክትባቱ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በትምህርት፣ በጤና ተቋማት እና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እየተሰጠ ይገኛል።
የጋምቤላ ክልል የጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ኡቦንግ ኜል በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች ከ42 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ ታዳጊ ሴቶች ክትባቱ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴር የክትባት ከፍተኛ ባለለሙያ የሆኑት አቶ ደብረወርቅ ጌታቸው በበኩላቸው፤ የማህፀን ጫፍ ካንሠር መከላከያ ክትባት እንደ ሀገር በሁሉም ክልሎች ከሰባት 7.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ታዳጊ ሴቶች እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
ክትባቱ ላለፉት 6 ዓመታት ስኬታማ በሆነ መልኩ መሰጠቱን መናገራቸውን ሪፖርተራችን ሚፍታህ አብዱልቃድር ዘግቧል።
በተመሳሳይ ክትባቱ በአማራ፣በኦሮሚያ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተሰጠ መሆኑን ከክልሎቹ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በአማራ ክልል በዚህኛው ዙር የክትባት ዘመቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዩን ታዳጊ ሴቶች እንደሚከተቡ በመረጃው ተመላክቷል።
በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የማህፀን ጫፍ ካንሠር ቅደመ መከላከል ክትባት መሰጠት መጀመሩም ተጠቁሟል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በሁሉም አካባቢዎች ክትባቱ መሰጠት የተጀመረ ሲሆን፤ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ወልተጂ በጋሎ የክትባት መርሐ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።
በአፋር እና ትግራይ ክልል የማህፀን ጫፍ ካንሠር ቅደመ መከላከል ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
በአፋር ክልል ከ92 ሺህ በላይ ታዳጊ ሴቶች ክትባቱን እንደሚወስዱ ተገልጿል።
በትግራይ ክልል ከ260 ሺህ በላይ ታዳጊ ሴቶች ክትባቱን ይወስዳሉ ተብሏል።
የማህፀን በር ካንሰር በኢትዮጵያ በገዳይነቱ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ እንደሚገኝና በየዓመቱ ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች በዚሁ በሽታ እንደሚያዙ መረጃዎች ያመለክታሉ።