ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህር ዳር ከተማ የመጀመርያውን ዙር የ3 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት የስራ ሂደትን ጎብኝተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፤ የመጀመርያ ዙር የባህር ዳር የኮሪደር ልማት ስራን ለማጠናቀቅ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱን ለማጠናቀቅ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አጠቃላይ 22 ነጥብ 5 ከሎ ሜትር የሚሸፍነው የኮሪደር ስራ በዚሁ ትጋት ከተሰራ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጉብኝቱን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍም፤ የኮሪደር ልማት የጣና ዳር ፈርጧ ባህርዳርን ተጨማሪ ውበት የሚያላብሳት ከመሆኑም በተጨማሪ ለነዋሪዎቿ፣ ቱሪስቶች እና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች የምትመች የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
በጥቂት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ የታሰበው የመጀመርያው ዙር የኮሪደር ልማት ቀን ከሌት በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ስራው በተጀመረው ትጋት እና ብርታት ተጠናቆ ሳይክል መጠቀም ባህላቸው ለሆነው የከተማይቱ ነዋሪዎች ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን አይተናል ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት የከተሞች ውበት እና የተጥሮ ሀብት ተጠብቆ እንዲዘምኑና የቱሪስት መስህብነታቸው እንዲጨምር በትኩረት መስራቱን እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
የባህር ዳር ከተማ የመጀመርያው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ ታህሳስ መጀመሪያ ላይ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአሸናፊ እንዳለ