የፈረንሳዩ ምግብ ማቀነባበሪያ ዴላሞት ኢንተርፕራይዝ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድረው ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የደረቅ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለጿል፡፡
የኢዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የኩባንያው ባለቤቶች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ኢትዮጵያ የስንዴ ምርቷን ለማሳደግ ከፍተኛ ስራ እየሰራች ባለበት እና ሀገሪቱ በበጋ እና በመኸር ስንዴ ምርት ፍላጎቷን ከሟሟላት አልፋ ለውጪ ሀገር ገበያ ልታቀርብ ስራ በጀመረች ወቀት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የተፈጠረው የስንዴ ምርት አቅርቦት መስተጓጎል ተጽእኖ እንዳያሳርፍባት መንግስት ቀድሞ በወሰደው ፈጣን እርምጃ ሀገሪቱ ከውጪ ስንዴ ለማስገባት ታወጣ የነበረውን ከ750 ሚሊየን ዶላር በላይ በሀገር ውስጥ መተካት መቻሏን ጠቅሰዋል፡፡
ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለመስራት ላሰበው ጣፋጭና ደረቅ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በዋናነት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች ውስጥ ስንዴ፣ የቅባት እህሎች እና የእንስሳት ተዋጽኦ መሆናቸውን የኩባኒያው መስራች ሴባስቲያን ዴላሞት አብራርተዋል፡፡
ኩባንያው ለሚያመርተው ምርት ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን ከኢትዮጵያ ከመጠቀም በተጨማሪ በዘርፉ ያካበተውን ቴክኒካል እውቀት ለኢትዮጵያ ባለሞያዎች በማስተለለፍ ለሀገራዊ ክህሎትና እወቀት መዳበር የበኩሉን ሚና መጫወት እንደሚፈልግም የኩባንያው መስራች መናገራቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡