የመጀመሪያውን የረቂቅ ሙዚቃ ትምህርት ተምረው ከመጡት ውስጥ ግንባር ቀደሙ ሰው፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ትምህርት ታሪክ ማስጀመርያ መሰረት ይሏቸዋል የሙዚቃ ባለሞያው እና የዛሬው የኢትዮጵያ አይዶል ዳኛ ሰርፀ ፍሬስብሃት።
ለዛሬ የሀገራችን የሙዚቃ ዕድገት ትላንት ላይ ሆነው እሩቅ ተመልክተው ሰርተዋል። ለዚህም ነው በጊዜው ብሄራዊ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመክፈት 7 ክፍሎችንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመዋስ ማስተማር የጀመሩት በማለት ያስረዳሉ የሙዚቃ ባለሞያው።
በዚህ የማስተማር ጥረት ውስጥ ሀገራችን ትልቅ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንደሚያስፈልጋት አይተውና ወጥነው ነበር። ይህን ውጥናቸውንም የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲመሰረት በማድረግ አስምረውታል።
የሀገራችን የሙዚቃ ዘርፍ ትልልቅ የምርምር ስራዎች እጥረት አለበት የሚሉት ሰርፀ ፍሬ ስብሀት እሳቸው ይህንን በመመልከት በሀገራቸውና በአህጉራቸው ሙዚቃ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጹሁፎችን ጽፈዋል።
እኝህ ሰው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ናቸው። ለመሆኑ እኚህ ሰው ምንድነው ያበረከቱት አስተዋጽዖ? በጥቂቱ እንመልከት።
የረቂቅ ሙዚቃው ሊቅ ትልቁን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሆነውን ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት በማቋቋም ስማቸው በጉልህ የሚነሳ፣ የባለዋሽንቱ እረኛ ሙዚቃ ፈጣሪ፣ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም ተወለዱ።
አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው ሲሆኑ የሙዚቃ ፍቅር ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲያድርባቸው ያደረጓቸው ደግሞ እናታቸው ወ/ሮ ፈንታዬ መሆናቸው ይነገራል።
መሰረታዊ የሚባለውን ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት እና በቀዳማዊ ኃይላ ሥላሴ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት (ኮከብ ጽባሕ) ካጠናቀቁ በኃላ በሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል።
ከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በኒው ዮርክ ከሚገኘው የሮቼስተር ዩኒቨርሲቲ "ኢስትማን የሙዚቃ ት/ቤት 1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትን መሠረቱ።
የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወ.ወ.ክ.ማ) በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት የዓይነ-ስውራን ት/ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማህበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።
የያሬድ ት/ቤት ዳይሬክተር ሆነው ከ 1955 እስከ 1958 ዓ.ም ድረስ ባገለገሉበት ወቅት በንጉሠ ነገሥቱ "ብሔራዊ የሙዚቃ አቀናባሪ" ተብለው ከመሠየማቸው ሌላ ለባህላዊ ጉዳዮች ላደረጉት የላቀ አስተዋፅዖ በ1954 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ተሸላሚ ሆነዋል።
የቀ.ኃ.ሥ የ75ኛ የልደት በዓል በተከበረበት በዚሁ ዓ.ም በሀንጋሪ መንግሥት ተጋብዘው ወደ ቡዳፔስት በመጓዝ የሚታወቁበትን “እረኛውን ባለዋሽንት” እና “ኢትዮጵያ ሲንፎረያ” የተባሉትን ሁለት ድርስቶቻቸውን በአቀናባሪነት በኦርኬስትራ መሪነት አቅርበዋል፣ በሸክላም አሳትመዋል።
ታዲያ በጉርምስና እድሜያቸው በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋውን “እረኛው ባለዋሽንት” የሚል መጠርያ የሰጡትን ረቂቅ ሙዚቃ ደረሱ። ደርሰውም አላበቁም በሀንጋሪ ፊሊሀርሞኒ ኦርኬስትራ ለህዝብ ለማስደመጥ ወደ አዳራሹ አቀኑ።
ታዲያ ሀንጋሪያውያን በጥቁሩ የረቂቅ ሙዚቃ አዘጋጅና “ኮንዳክተር” ላይ ሊስቁ ወደ አዳራሹ ተመሙ። እንስቃለን እንሳለቃለን ብለው ወደአዳራሹ የገቡት ሃንጋሪያውያኑ በፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ስራ ተደንቀው እጃቸውን በአፋቸው ጭነው በሀገራቸው በጊዜው ታዋቂ በነበረው ሙዚቀኛ “ኮዳይ” ስም ይጠሯቸው እና ያደንቋቸው ተያያዙ።
“ጥቁሩ ኮዳይም" በሀንጋሪ የፕሮፌሰሩ መጠርያ ሆነ።
ለወትሮው በረቂቅ መሳርያ የተቀነባበረ ሙዚቃ በአውሮፓውያን ዘንድ ብቻ ተወዳጅ ሆኖ ይሳል ነበር። ነገር ግን የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ "እረኛው ባለዋሽንት" ሥራ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለጥሞና የሚደመጥ፣ የፕሮግራም ማጀቢያ በመሆን አየር ላይ በመዋል ለዘመናት ተወዳጅነትን ያተረፈ ረቂቅ ሙዚቃ ለመሆን በቃ።
ብዙዎች "እረኛው ባለዋሸንት" የተሰኘው ሙዚቃ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደዚህ እንዲወደድ ያደረገው ፕሮፌሰር አሸናፊ በሀገረኛ ለዛ ስላዘጋጁት ነው ብለው ያምናሉ።
እውነት ነው እኝህ የሙዚቃ ሊቅ ለሀገርኛ የሙዚቃ እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ናቸው። ከእረኛው ባለዋሽንት በተጨማሪም፦
የኢትዮጵያ ሰላም
የፍቅር አንሰር
የሳት እራት
የተማሪ ፍቅር
የሀገራችን ሕይወት
ኒርቫኒክ ፋንታሲ የተሰኙ ረቂቅ ሙዚቃዎችን ለአድማጭ ጆሮ ያደረሱ የሙዚቃ ደራሲ አቀናባሪና ኮንዳክተር ናቸው።
እናታቸው በሚጫወቱት በገና ተማርከው ወደ ሙዚቃው አለም እንደገቡ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፤ ሙዚቃን ከሰው ልጅ አኗኗር ጋር በሚያጠናው “ኢትኖሚውዚኮሎጂ” ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።
ከአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ጀምሮ በረዳት ፕሮፌሰርነት የኢትኖሚውዚኮሎጂ ፕሮግራም ዳይሬክተር በመሆን በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ "ኪዊንስ ኮሌጅ እና በማሳቹሴትስ ብራንዲስ ዩኒቨርስቲ” በረዳት ፕሮፌሰርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድርስ ለ19 ዓመታት በፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ መጀመሪያ በፕሮፌሰርነትና በኋላም የዩኒቨርስቲው "የጥቁር አሜሪካውያን የባህል ማዕከል" ዳሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
የሙዚቃ ደራሲና አቀናባሪው ፕሮፌሰር አሸናፊ የሙዚቃ ሰዋሰው የመማርያ መፅሀፍ በአማርኛ፣ ኮንፌንሽን ልቦለድ እንዲሁም Root of Black Music የተሰኙ መጽሐፍትም ለአንባቢያን አድርሰዋል።
የሙዚቃ ሊቁ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ በ1990 ዓ.ም በ 60 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ታዲያ እኝህ የሙዚቃ ሊቅ በማቋቋም ረገድ ትልቁን ሚና በተጫወቱበትና በመጀመርያ ዳሬክተርነት ባገለገሉበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በስማቸው የተሰየመው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የፐርፎርሚንግ አርት ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወሳል።
ከዓለም የሙዚቃ ቀማሪዎች ቀድሞ ሙዚቃን ያወቀ እና የቀመረው ቅዱስ ያሬድ በዓለም ዘንድ በስራው ልክ የሚታወቅ አይደለም። ይሁን እንጂ በስራው ደግሞ ዛሬም የሚያበራ ኮኮብ እንደሆነ ነው። በዚህ ድንቅ እና ቅዱስ ሰው ስም የተሰየመው የሙዚቃ ትምህርት ቤትም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደም ድንቅ ስራ ሰርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) “ሙዚቃ የማይታይ ነገርን ማሳየት ነው፤ ያልገባን ነገር እንዲገባን ማድረግ ነው” ብለዋል። ለዚህም ወደኋላ በአንድ ዐይን መመልከት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅዱስ ያሬድ ስም የተሰየመ ትምህርት ቤት አለን ብሎም ይህ ማዕከል ደግሞ በታዋቂው የረቂቅ ሙዚቃ ባልሞያው ስም ተስይሟል ብለዋል። ይህ በአንድ አይን ወደኋላ መመልከት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ደግሞ የኋላውን አይቶ ወደፊት ማሻገር እነድሚገባ እና ለዚህም አሁን ላሉ ባለሞያዎች አደራ ብለዋል።
የአንጋፍው የሙዚቃ ትምህርት ቤት የመጀመርያው ዳሬክተርና የሙዚቃ ሊቅ የነበሩት ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፉ እና ዘመን አይሽሬ ሥራዎችንም ያበረከቱ ሊቅ እንደሆኑ በትውልድ ውስጥ ተቀምጠው ይኖራሉ።
በዚህ ታሪካዊ ማዕከል ዛሬ ታሪካዊው እና አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ አይዶል የፍጻሜ ውድድሩን እያካሄደበት ነው ፡፡
በታሪካዊው ማዕከል ታሪካዊ አሸናፊ የሚለይበት ቀን ዛሬ እየተከናወነ ሲሆን አንደኛ የሚወጣው ተወዳዳሪ 1 ሚሊየን ብር ይሸለማል።
ማን ያሸንፍ ይሆን?
ሚኪያስ ጌቱ (E4)
ማቲያስ አንበርብር (E3)
ዩሐንስ አምደወርቅ (E2)
ብዙዓየሁ ሰለሞን (E1)
#የኢትዮጵያአይዶል #ኢትዮጵያ #አይዶል #etv #EBC #ebcdotstream #Ethiopia #musicaa #ethiopianidol
በናርዶስ አዳነ