ኢቢሲ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ተገኝቶ የዘገባ ስራዎችን ለመከወንና የይዘት ስራዎችን መልሶ ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ሲሉ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ የተገነባው የኢቢሲ ተጨማሪ የይዘት ምንጭ ወላይታ ሶዶ ስቱዲዮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።
በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ፤ የክልሉን ህዝብ በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ህዝቡ መናገሪያ መድረክ ሚዲያ እንዲያገኝ የስቱዲዮው መገንባት ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው አዲስ የተመረቀው የኢቢሲ ወላይታ ሶዶ ስቱዲዮ ግንባታ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ላስቻሉት ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከባዱን ስራ በጣም ቀለል በሆነ መንገድ ስቱዲዮውን ሰርተን ለምርቃት እንድናበቃ ስላደረጉን እናመሰግናለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች ያሉ አመራሮች ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመራሮች ትምህርት መውሰድ እንደሚገባቸውም አቶ ጌትነት በንግግራቸው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮሮፕሬሽን ብሄራዊ ጣቢያ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ እንደ ብሄራዊ ጣቢያነቱ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ተገኝቶ የዘገባ ስራዎችን መስራት፣ የይዘት ስራዎችን መልሶ ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡
በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ልንደርስበት የሚገባውን መሻታችንን ለማሳካት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት በአፍሪካ ደረጃ መደመጥ የሚገባን ህዝቦች ነንና አመራሩ በየደረጃው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በኢቢሲ የወላይታ ሶዶ ስቱዲዮ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና ከተለያየ ክልሉ የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ