ቤኑና መንደር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ሀገርን በትጋት ለመለወጥ ትምህርት የሚወሰድበት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

1 Mon Ago 428
ቤኑና መንደር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ሀገርን በትጋት ለመለወጥ ትምህርት የሚወሰድበት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቤኑና መንደር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ሀገርን በትጋት ለመለወጥ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበሰቃ ሀይቅ ላይ የተገነባውን ቤኑና መንደርን መርቀው ከፍተዋል።

ቤኑና መንደር በበሰቃ ሃይቅ ዳርቻ እጅግ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች፣ አዳራሽ፣ ሲኒማ ቤት የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ስፓ፣ እንዲሁም የፍራፍሬ ልማት እና የሌማት ትሩፋትን አካቶ የያዘ ነው።

የመንደሩ ግንባታም ባህላዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብን ከዘመናዊ ግንባታ ጋር አቀናጅቶ የያዘ ሲሆን፣ ለአካባቢው ተጨማሪ የቱሪዝም አቅም የፈጠረ ወብ መዳረሻ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንደሩን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቤኑና መንደር ይቻላልን በአይናችን ያየንበት ነው ብለዋል።

አካባቢው በጣም አስቸጋሪ የአየር ጠባይና መልክዓ ምድር እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህን በመቋቋም ውብ ገጽታ ያለውን መንደር እውን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

ይህም ፈተና ኢትዮጵያን ከመቀየር እንደማያቆመን ዳግም ያረጋገጥንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

መንደሩ ከመዝናኛ ስፍራዎች በተጨማሪ የፍራፍሬ ልማትና የሌማት ትሩፋትን ማካተቱ ደግሞ ግብርናን ከቱሪዝም መዳረሻ ጋር ለማስተሳሰር ትምህርት የሚወሰድበት ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በመንደሩ የብርቱካን፣ የሎሚ፣ የፓፓዬና የማንጎ ልማት እንዲሁም ዶሮ፣ ግመል፣ ከብትና ፍየል የማርባት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የቤኑና መንደር ግንባታም በኢትዮጵያ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት ትብብር የተከናወነ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የስካይ ላይት ሆቴል መንደሩን ተረክቦ የማስተዳደር ስራ እንደሚያከናውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው አስታውቀዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top