የጥራት መንደር የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ አብሳሪ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

20 Days Ago 276
የጥራት መንደር የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ አብሳሪ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የጥራት መንደር ለዘላቂ እድገት መሰረት የሚጥልና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ ያበሰረ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተደራጀውን የጥራት መንደር መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡

የጥራት መንደሩ የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅትን ያካተተ ነው፡፡

የጥራት መንደሩ የተቀናጀና ደረጃውን የጠበቀ የጥራት አግልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲሆን፤ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በብዛት የማይገኙ የሴራሚክ፣ የባትሪ እና የሶላር ሀይል ማመንጫ መፈተኛ መሳሪያዎችን ለመፈተሽ የሚያስችሉ ላብራቶሪዎችን ጭምር ያካተተ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ የጥራት መሠረተ ልማት ለዘላቂ ዕድገት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ጥራት ያለው ምርትን ወደ ውጭ በመላክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚያስችል ነው ያነሱት፡፡

ጥራት ከዜጎቻችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተሳሰረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከዚህ አኳያ የጥራት መንደሩ ደረጃቸውን የጠበቁና ጤናማ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የጥራት መንደሩ እጅግ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውና በኢትዮጵያ ምርቶች ወጪ ንግድ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ስለመሆኑም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡

በዚህም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ ያበሰረ መሰረተ ልማት መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጥራት መንደሩ በፊዚክስ እና ተያያዥ የጥናት ዘርፎች ዝንባሌ ያላቸው ታዳጊዎችን ለማፍራትም ተጨማሪ ዕድል ይዞ መምጣቱን አውስተዋል።

ከዚህ አኳያ ወላጆች ልጆቻቸው የጥራት መንደሩን እንዲጎበኙ በማድረግ ታዳጊዎች ከወዲሁ ፊዚክስ እንዲሁም የቴክኖሎጂና የምርምር ዝንባሌ ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top