ኢትዮጵያ የሰላም አማራጭን በማጽናት በመተማመን ላይ የተመሰረተ አጋርነትን ለማጠናከር ትልቅ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የብሔራዊ ተሀድሶ የቦርድ ሰብሳቢ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ሥልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት በመቐለ ከተማ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል።
በሥነ-ሥርዓቱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄነራል ፃድቃን ገብረ-ትንሳኤና የብሔራዊ ተኃድሶ ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁንን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የብሔራዊ ተሃድሶ የቦርድ ሰብሳቢ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ የውስጥ ችግሮች እንዳጋጠሟት ተናግረዋል።
በተለይም ከግጭት ጋር በተያያዘ ባጋጠሙ ችግሮች አገሪቱ በበርካታ ፈተና ውስጥ እንድታልፍ ማስገደዱን ጠቅሰው፤ ይህም በርካታ ሰብዓዊ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል።
ግጭት ኪሳራው የበዛ እንዲሁም ጠባሳው በቀላሉ የማይጠፋ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ አስከፊውን የግጭት አዙሪት በማቆም ለሰላማዊ አማራጭ ፊቷን በማዞር አንድ ምዕራፍ ወደፊት እየተራመደች ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚህም ሰላምን በማጽናት በመተማመን ላይ የተመሰረተ አጋርነትን በማጠናከር ትልቅ እርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል።
በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በማቆም ችግሩን በሰላማዊ አማራጭ እልባት እንዲያገኝ እገዛ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የሂደቱን ውጤታማነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ከትግራይ ክልል በተጨማሪም በመላ ኢትዮጵያ በነፍጥ ፋንታ ሞፈር፤ በታንክ ፋንታ ትራክተር የሚገንበትና የሰላምና ልማት ዘመን እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በታሪክ ውርስ ሲተላለፍ የመጣውን የግጭትና የጦርነት ባህልና አዙሪትም በሰላማዊ አማራጭ በመዝጋት ቀጣዩን ለትውልድ የሰላምና የልማት፣ የውይይትና የምክክር ባህል ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ የታደሙ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአሕጉራዊና ዓለም አቀፍ ተወካዮችም የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ሥልጠና ለመስጠት የተደረጉ የዝግጅት ሂደቶችንና በመቐለ ዩኒቨርሲቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል።