ፍቺን የሚያወግዘው የካሮ ብሄረሰብ

20 Days Ago 368
ፍቺን የሚያወግዘው የካሮ ብሄረሰብ

የካሮ ብሄረሰብ በደቡብ ኦሞ አካባቢ የሚገኝ ማህበረሰብ ሲሆን አነስተኛ የህዝብ ብዛት  ያለው ነው፡፡

በኦሞ ዳርቻ አካባቢ የሚገኙት እነዚህ ማህበረሰቦች የህዝብ ብዛታቸው እስከ 2 ሺህ ገደማ እንደሆነም ይገመታል፡፡

ካሮ በኢትዮጵያ የኦሞን ወንዝ ተፋሰስ ተከትለው ህይወታቸውን ከመሰረቱ ማህበረሰቦች መካከልም ይጠቀሳሉ።

ካሮዎች የኦሞ ወንዝን ተመርኩዘው የተለያዩ እንደ ማሽላ፣ በቆሎ የመሳሰሉ እህሎችን አምርተው የሚመገቡ ሲሆን፤ በብዛትም ፍየሎችን በማርባት ይታወቃሉ፡፡

አርማቸው እና መታወቂያቸው ሰውነታቸው ላይ የሚቀቡት በነጭ ቀለም የተዋበ ጥበባቸው ሲሆን ቀለሙንም እራሳቸው እንደሚቀምሙትም ይነገራል፡፡

የተለያዩ ቀለማት ባላቸው የማዕድን ድንጋዮች እና የቾክ ድንጋይ በመጠቀም ውህዱን ይሰሩታል፡፡

የካሮ ማህበረሰቦች ከኛንጋቶም፣ በና፣ በሻዳ፣ ሀመር ከመሳሰሉ ማህበረሰቦች ጋር ጉርብትና አላቸው።

በተለይም የካሮ ሴቶች ለውበታቸው የተለየ ቦታ ስላላቸው ቀለማቱን በመጠቀም ለውበት መገለጫም ይጠቀሙታል፤ የወንዶቹ ንቅሳት ከውበት ይልቅ የጀግንነት መገለጫ  እንደሆነም የአከባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡

ቀለሙን ቀብተው ደረታቸው ላይ ሲያደርጉ ዝንጀሮን፣ አንበሳ፣ ጅብና መሰል የዱር እንስሳትን ለመከላከል እንደሚነቀሱትም ይናገራሉ፡፡

ፊታቸው ላይ የሚቀቡት ነጭ ነገር ከጉሬዛ መሰል የዱር እንስሳት ጋር ለመመሳሰል እንደሚጠቀሙት ይጠቅሳሉ፡፡

ወንዶች ሙሉ አካላቸውን ነጭ ቀለም ሲቀቡ፤ ሴቶቹ ግን ፊታቸውን አልፎ አልፎ ደግሞ እጃቸውን እንደሚቀቡም የአከባቢው ነዋሪ የሆኑት ባኖ ሻፎ በተለይ ለኢቲቪ አስረድተዋል፡፡

በትዳር አመሰራረታቸው ወንዶች በህይወታቸው አንድን ሴት ካጩ በኃላ ለልጅቷ ቤተሰቦች 127 ፍየሎች በጥሎሽ መልክ ይሰጣሉ፡፡

"በካሮ ብሄረሰብ ዘንድ ጥንዶች ከተጋቡ በኋላ መፋታት የሚባል ነገር በባህሉ አይታወቅም" የሚሉት የአከባቢው ነዋሪው፤ ችግሮቻቸውን ተነጋግረው እንደሚፈቱ ጠቅሰዋል፡፡

በቦታው ላይ በርከት ያሉ ቱሪስቶች የካሮ ብሄረሰብ ባህልና እሴት ለመመልከት ከተለያዩ ዓለም ሀገራትም ይመጣሉ፡፡

በአስገራሚ የጋብቻ ስነ-ስርዓታቸው የሚታወቁት የካሮ ብሄረሰቦች በቱሪስቶችም በጣም ተወዳጆች ናቸው፡፡

ቱሪስቶቹ በሚያዩአቸው ለምለም ስፍራዎች፣ በአከባቢው ነዋሪዎች አለባበስ እንዲሁም በጋብቻ ሁኔታቸው ሁሉ እንደሚደነቁ ይነገራሉ፡፡

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top