የጥራት ደረጃ ምልክቶችን በምርት ላይ ማስፈር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አስገዳጅ እንደሆነ ያውቃሉ?

15 Days Ago 183
የጥራት ደረጃ ምልክቶችን በምርት ላይ ማስፈር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አስገዳጅ እንደሆነ ያውቃሉ?
የምርት ጥራት ደረጃ ምልክቶች እንዴት ይሰጣሉ?
 
ከEBC DOTSTREAM ጋር ቆይታ ያደረጉት በጥራት መንደር ውስጥ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የማርኬቲንግና ኮምኒኬሽን ዳሬክተሩ አቶ ተኬ ብርሀነ ለዚህ መልስ አላቸው።
 
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በምርቶችና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት የሚሰጥ የመንግስት ተቋም ነው።
 
ድርጅቱ የጥራት ማረጋገጫውን ሲሰጥም ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካትታል ብለዋል አቶ ተኬ፤ የመጀመርያው የፍተሻ ላብራቶሪ አገልግሎት ሲሆን ሁለተኛው ምርመራ እና የመጨረሻው ደግሞ ሰርተፍኬት መስጠት ናቸው።
 
ተቋሙ የሰርተፍኬት አግልግሎት ሲሰጥ የተለያዩ ምልክቶችን ይጠቀማል የሚሉት ዳሬክተሩ፤ የሚጠቀማቸው ምልክቶችም ምርቶቹ የጥራት ማረጋገጫ እንዳላቸው የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።
 
ምልክቶቹ ሁሉም ፍተሻ የተደረገባቸው ምርቶች ላይ እንዲታዩ ተደርገው እንደሚቀመጡ ገልጸው፤ ምርት የሌለው ሲስተም ወይም አገልግሎት ብቻ ከሆነ ደግሞ ለአገልግሎታቸው ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል ነው ያሉት።
 
አገልግሎቱን የሚሰጡት አካላትም ለተገልጋዩ ያገኙትን የጥራት ደረጃ ሰርተፍኬት ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
 
እነዚህ የጥራት ደረጃ ምልክች አንድ ምርት የኢትዮጵያን ደረጃ አሟልቶ ገበያ ላይ ሲውል የሚሰጡ የጥራት ማረጋገጫ መሆናቸውን ተናግረዋል።
 
ምልክቶቹ የተደረጉባቸው ምርቶችም ሆኑ አገልግሎቶች ጥራት እንዳላቸው የተመሰከረላቸው ማረጋገጫ የተሰጣቸው ስለሆኑ፣ እነዚህን የምርት ጥራት ደረጃ ምልክቶች ያሉባቸውን ምርቶች ተጠቃሚዎች ያለምንም ስጋት መጠቀም እንደሚችሉ ነው የገለጹት።
 
አንድ ተጠቃሚ አንድ እቃ አገልግሎቱ ያላለፈበት ወይም "ኤክስፓየርድ ዴት" አይቶ እንደሚገዛው ሁሉ ምርቶቹ ጥራት እንዳላቸውና እንደሌላቸው አረጋግጦ ሊጠቀም ይገባዋል ይላሉ።
 
ሰርተፍኬትም ሆነ የምርት ጥራት ደረጃ ምልክት (የጥራት ማረጋገጫ) የለኝም የሚሉ አገልግሎት ሰጭዎች ካሉ እነሱ ጥራት የሌለው ምርት ይዘዋል ብሎ ለመደምደም እንደሚያስገድድ አቶ ተኬ ብርሀነ ገልጸዋል።
 
አንድ ምርት አቅራቢ ወይም አገልግሎት ሰጪ ምልክቱን ምርቱ የሚታይ ቦታ ላይ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፣ የማይመች ምርት እንኳን ቢይዝ ሰርተፍኬቱን ለተጠቃሚዎች የማሳየት ግዴታ አለበት ሲሉም አክለዋል።
 
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በጥራት መንደሩ ውስጥ ካሉ 5 ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡም ሆነ የሚወጡ ምርቶችን የምርት ጥራትን ከሚለኩ ድርጅቶች ውስጥ አንደኛው ነው።
 
በናርዶስ አዳነ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top