የፓን አፍሪካኒዝም ምልክት እና የአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለያዩ ሀገራት አየር መንገዶችን ድርሻ በመያዝ በአህጉሪቱ ቀዳሚነቱን እያሰፋ ይገኛል።
የፓን አፍሪካን ኔትዎርክ መፍጠር እና ማጠናከር ዓላማው የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በአራቱም ማዕዘናት በማስተሳሰር የአፍሪካውያንን እርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እየሠራ ይገኛል።
አየር መንገዱ በቪዥን የ2025 ስትራቴጂው አፍሪካን የማስተሳሰር በአፍሪካ ያለውን የገበያ ድርሻ ለማሳደግ ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል አንዱ ከአህጉሪቱ አየር መንገዶች ጋር በትብብር መሥራት ነው፡፡ ይህም ስትራቴጂያዊ ሽርክና፣ የጋራ ባለቤትነት እና የአስተዳደር ስምምነቶችን መፍጠርን ይጨምራል።
በዚህም መሰረት በርካታ የአህጉሪቱ አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለው የዳበረ ልምድ እንዲያደራጃቸው እና ድርሻውንም እንዲይዝ ፍላጎታቸውን ማሳየት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ አየር መንገዱም የተመረጡ አየር መንገዶችን ከ40 እስከ 49 በመቶ ድርሻ ይዞ መልሶ የማደራጀት ሥራውን ቀጥሏል፡፡
አየር መንገዱ በዚህ መንገድ ካደራጃቸው አየር መንገዶች መካከል "ኤርስካይ" የተሰኘው የቶጎ አየር መንገድ አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርስካይ አየር መንገድን 40 በመቶ ድርሻ ይዞ እንደገና ያደራጀው እ.አ.አ በ2010 ነው፡፡ መነሻውን ሎሜ ቶጎ ያደረገው ‘ኤርስካይ’ በምዕራብ አፍሪካ ያሉ ሀገራትን ለማስተሳሰር ይሠራል፡፡ በዚህ መነሻም ከሀገር ውስጥ በረራ በተጨማሪ ከ20 በላይ ወደሚሆኑ የምዕራብ እና መካከለኛ አፍሪካ ሀገራት በረራውን ያደርጋል፡፡
የማላዊ አየር መንገድ ሌላው በኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ እ.አ.አ በ2013 መልሶ የተደራጀ አየር መንገድ ነው፡፡ ቀድሞ የነበረው የማላዊ አየር መንገድ ከአገልግሎት ውጭ ከሆነ በኋላ ነው በማላዊ መንግሥት ጥያቄ አየር መንገዱ እንደገና የተመሰረተው፡፡ የማላዊ መንግሥት 51 በመቶ ድርሻውን የያዘ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአስተዳደር፣ የአቅም ግንባታ እና ሌሎች ቴክኒካዊ ሥራዎችን በኃላፊነት ይሠራል፡፡
