ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአየር ንብረት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያቀርቡትን የፋይናንስ መጠን ሊያሳድጉ ይገባል - አቶ አሕመድ ሽዴ

3 Hrs Ago 22
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአየር ንብረት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያቀርቡትን የፋይናንስ መጠን ሊያሳድጉ ይገባል - አቶ አሕመድ ሽዴ

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለአየር ንብረት ለውጥ እና የልማት ስራዎች የሚያቀርቡትን የፋይናንስ መጠን መጨመር እንደሚገባቸው የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ገለፁ።

አማራጭ የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ትኩረቱን ያደረገው 22ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል።

ስብስባው የተካሄደው ከዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዓመታዊ ስብስባዎች ጎን ለጎን ነው።

ስብስባውን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ክዋካ በጋራ መርተውታል።

ውይይቱ ፈተናዎችን በመቋቋም ባሉ ቁልፍ ጉዳዮች እና አማራጭ ፋይናንስ አማራጮችን በማስፋት በቀጣናው ዘላቂ ልማት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ግቦችን ለማሳካት የጋራ ትብብር እና አጋርነትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን በውይይቱ ላይ አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።

ሚኒስትሩ በቅርቡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል የቀጣናዊ ልማት፣ ትስስር እና የንግድ አቅርቦት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙትን  ኔና ንዋቡፎን እንዲሁም አዲሶቹ የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን የፋይናንስ ሚኒስትሮች ወደ ኢኒሼቲቩ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።

የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች አጋሮች ለኢኒሔቲቩ እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት (BADEA) ኢኒሼቲቩን ለመደገፍ ያሳየውን የትብብር ፍላጎት አንድንቀዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅድ እና በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት የሚመደበው የፋይናንስ መጠን ሊያድግ እንደሚገባ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ሰዓት ለጉዳዩ እየቀረበ ያለው የፋይናንስ መጠን በቂ አለመሆን አንስተዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ሌሎች አጋር አካላት በጋራ በመሆን በአየር ንብረት ለውጥ እና ፋይናንስ አቅርቦት ያሉ ፈተናዎችን መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ኢንቨስትመንቶች በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ዘላቂ የእዳ አስተዳደር በማይነካ መልኩ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የተለያዩ አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በዚህ ረገድ ያላቸው ሚና ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።

በውይይቱ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አማራጭ የፋይናንስ አቅርቦትን የሚያሳድጉ ተጫባጭ ስትራቴጂዎችን መቅረጽ እና የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ጥረቶችን ማጎልበት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የፋይናንስ አቅርቦቱ እንዲሰፋ ከተለመዱ የሀብት ማፈላለጊያ መንገዶች ውጪ አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ እ.አ.አ በ2019 የተቋቋመ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የኢኒሼቲቩ አባል አገራት ናቸው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top