የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንመክራለን፡- የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ

1 Day Ago 87
የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንመክራለን፡-  የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ በ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል። 

ፕሬዚዳንቱ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር)፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት ኢሳያስ ጂራ፣ የካፍ የኢትዮጵያ ተወካይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ በተለይ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ ለ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

በቆይታቸውም የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እንደሚመክሩም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ኮንጎ ብራዛቪል በገጠማት ወረርሽኝ ምክንያት ማስተናገድ ያልቻለችውን ጉባኤ ማዘጋጀቷ፣ ሀገሪቱ ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት የምታደርገውን ጥረት አጉልቶ ያሳያልም ተብሏል።

ለዚህ ጉባኤ የአዲስ አበባ ምርጫ ከተማዋ በአፍሪካ ስፖርት ላይ ያላትን ተፅእኖ እና ዋና ዋና አለም አቀፍ ዝግጅቶችን የማስተናገድ ብቃቷን ያሳያል። 

የ46ኛው የካፍ ጉባኤ ከተለያዩ አባል ማህበራት ተወካዮች መካከል የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ውይይቶች እና የአህጉሩን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣት በሚቻልበት  ሁኔታ ላይ ይመክራል።

ጠቅላላ ጉባኤው የአፍሪካ እግር ኳስን የሚመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮችን ለአብነት የስፖርቱ የልማት ስትራቴጂዎች፣ የአስተዳደር ጉዳዮች እና ቀጣይ አህጉራዊ ውድድሮች ቅድመ ዝግጅቶችን ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል። 

ጉባኤው በአፍሪካ የእግር ኳስ ደረጃን ከፍ ለማድረግ በሚደረገው የትብብር ጥረት ላይ አባል ማህበራት እንዲወያዩበት እድል ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የካፍ ፕሬዚዳንት እና ሌሎች ቁልፍ ሰዎች መገኘታቸው እነዚህ ውይይቶች ስፖርቱን በአህጉሪቱ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለውን ጠቀሜታ አጉልቶ እንደሚያሳይም ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ የ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ሆና መመረጧ ሀገሪቱ በአፍሪካ የእግር ኳስ እድገትን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ትልቅ ክስተት ነው። 

ስብሰባው የአፍሪካን እግር ኳስ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ የሚያጎለብቱ አዳዲስ ጅምሮች እና አጋርነቶች መንገዱን ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።

46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ከነገ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ተከታታይ ቀናት በስካይ ላይት ሆቴል በተለያዩ ፕሮግራሞች የሚስተናገድ ይሆናል።

በወጋየሁ ሙሉነህ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top