የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ለመተግበር እና የቅድመ ማስጠንቀቅያ ስራዎችን ለመስራት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ ነች ሲሉ የኤፌዴሪ ፕሬዚደንት ታየ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
በአዘር ባጃን ባኩ እየተካሄደ ባለው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙት ፕሬዚደንት ታየ አጽቀሥላሴ፤ በፈረንጆቹ 2022 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት የተጀመረውን የቅድመ ማስጠንቅና የአደጋ መከላከል ስራ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ነው ብለዋል።
ቅድመ መከላከል ላይ ባተኮረው የውይይት መድረክ "ዛሬ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለማችን የጥፋት በትሩን እያሳረፈ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከዚህ በፊት ታይተው የማያውቁ የመሬት መንሸራተቶች እና የጎርፍ አደጋዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት እየተከሰቱ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ለዚህም የቅድመ ማስጠንቀቅ ስራዎችን መስራት እና ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ መከላከል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ተሳታፊዎች የዓለምን ሙቀት ከ1.5 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ እንዳይሆን ቅንጅታዊ አሰራር እና ድጋፍ ያስፈልገናል ብለዋል ፕሬዚደንት ታየ አጽቀሥላሴ።