አዲሱ የባንክ አሰራር ረቂቅ አዋጅ የፋይናንስ ዘርፉ ቀጣይነት ላለው የምጣኔ ሀብት እድገት ሚናውን እንዲወጣ ያግዛል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

1 Mon Ago 328
አዲሱ የባንክ አሰራር ረቂቅ አዋጅ የፋይናንስ ዘርፉ ቀጣይነት ላለው የምጣኔ ሀብት እድገት ሚናውን እንዲወጣ ያግዛል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

አዲሱ የባንክ አሰራር ረቂቅ አዋጅ የፋይናንስ ዘርፉ ቀጣይነት ላለው የምጣኔ ሀብት እድገት ሚናውን እንዲወጣ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት፣ ፕላንና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ እና ባንክ አሰራር ረቂቅ አዋጆች ላይ ከብሔራዊ ባንክ የስራ ኃላፊዎች ጋር የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።

በአስረጂ መድረኩ በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ግልጽነት ሊፈጠርባቸው ይገባል የተባሉ ጉዳዮች ተነስተው በባንኩ አመራሮች ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፣ ባንኩ የረዥም ዓመታት የኢኮኖሚና የፖለቲካ አደረጃጀቶች ዋና ዋና የሚባሉ የኢኮኖሚ ግቦችን በማሳካት ቁልፍ ሚና የተጫወተ ተቋም መሆኑን አስታውሰዋል።

ይሁንና ባለፉት 16 ዓመታት በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ለውጦች ቢኖሩም አዋጁ ሳይሻሻል መቆየቱን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ እያደገ የመጣውን የፋይናንስ ዘርፍ ግምት ውስጥ በማስገባትና የባንኩን ተዓማኒነትና ተጠያቂነት እንዲሁም የባንክ አስተዳደሩን ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር ለማጣጣም የባንክ አሰራር ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በረቂቅ አዋጁ የውጭ ባንኮችን ጨምሮ አዳዲስ ባንኮች ወደ ዘርፉ ሲቀላቀሉ ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ መስፈርቶችና የፍቃድ አሰጣጥ ሂደት የሚወስን መሆኑንም ነው ያነሱት።

 

በረቂቅ አዋጁ አዲስ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል በተለይም የፋይናንስ ዘርፉ ችግር ውስጥ ሲገባ ብሔራዊ ባንክ እልባት መስጠት የሚያስችለውን አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

ይህም የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማና ተወዳዳሪ ሆኖ ቀጣይነት ላለው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ሚናውን እንዲወጣ ያግዛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው አባላት በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ግልጽነት ይጎድላቸዋል ያሏቸውን ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን ተጨማሪ ማብራሪያና ማስተካከያ የሚያሻቸው አንቀፆች ላይም ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ባንኩ የሀገር ወስጥና የውጭ ምንዛሬ ኖቶችን ከውጭ ሲያስገባ ወይም ወደ ውጪ ሲልክ  የጉምሩክ ዲክላራሲዮን መሙላት እንደማይገደድ የሚጠቅሰውን አንቀጽ በማንሳት፤ ይህ የሆነበትን ምክንያት ጠይቀዋል፡፡

የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ በምላሻቸው ባንኩ በዋናነት ከውጭ የሚያስገባው የሚያሳትመውን ብር በመሆኑ የጉምሩክ ዲክላራሲዮን ማድረግ እንደሌለበት እና ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅም ይህን የተከተለ ተመሳሳይ አሰራር እንደነበረው ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በረቂቅ አዋጆቹ ላይ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ውይይት እንደሚያደርጉበት ተገልጿል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top