ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ትሰራለች - ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

1 Mon Ago 169
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ትሰራለች - ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገርን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትሩ የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያ በማኀበረ-ኢኮኖሚ መስኮች ለማሻሻል ለምታደርገው ጥረት ቁልፍ አጋር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደምትሰራ እና በተለይም በልማት ትብብር፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ግንኙነቱን ለማስፋት ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአምባሳደሯ በቀጣናው ስላለው ወቅታዊ የሰላም እና ፀጥታ ሁኔታ ገለጻ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ 22 የሕብረቱ አባል አገራት ተወካዮች እንደሚገኙ እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ጉልህ ስትራቴጂካዊ ሚና አኳያ ሕብረቱ ከአገሪቱ ጋር ላለው ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

አምባሳደሯ በኢትዮጵያ ከ180 በላይ የአውሮፓ ኩባንያዎች እንደሚገኙ በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኩባንያዎች የበለጠ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ ገንቢ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top