በትግራይ ክልል ዓዲ-ዳዕሮ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት በቃ

1 Mon Ago 191
በትግራይ ክልል ዓዲ-ዳዕሮ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት በቃ

በትግራይ ክልል የዓዲ-ዳዕሮ ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ተወካይ ኃላፊ ኢንጂነር ዮሃንስ መለሰ እንዳሉት፤ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው ዋን ዋሽ ኢንተርናሽናል ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በተገኘ 57 ሚሊዮን ብር ወጪ ነው።

ፕሮጀክቱ ከ6 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር በላይ የቁፋሮ እና የውኃ ቱቦ መስመር ዝርጋታ ሥራዎችን በማከናወን ለአገልግሎት እንዲበቃ መደረጉን ገልፀው፣ 18ሺህ 500 የሚሆኑ የዓዲ ዳዕሮ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የዋን ዋሽ ኢንተርናሽናል ተወካይ ኢንጂነር ቴዎድሮስ ታደለ በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው በክልሉ ያለውን የመጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመተባበር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የከተማዋ ነዋሪዎች ንፁህ ያልሆነ ውሃን ከወራጅ ወንዝ ለመቅዳት እስከ ሁለት ሰዓታት በእግር ይጓዙ እንደነበር የገለፁት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች አቶ ገብረ እግዚአብሄር ሀጎስ እና ዲያቆን ዘርዓይ አሰፋ ናቸው።

በመንግስትና በዋን ዋሽ ኢንተርናሽናል ጥረትም አሁን ችግራችን በመፈታቱ ምስጋናችን የላቀ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የውኃ ብክነት እንዳይኖር በመጠበቅና በስርዓት ውኃውን ለመጠቀም እንሰራለን ሲሉም ነው ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top