ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗን ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በ COP 29 ጉባኤ የአለም መሪዎች የተገኙበት የከፍተኛ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምግብ ስርዓት እና የተፈጥሮ ማገገም ላይ ያተኮረ ስብሰባ ላይ ተካፍላለች።
በስብሰባዉ የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የአየር ንብረት ለውጥ እና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አምና አል ዳሃክ እንዲሁም የCOP 29 ፕሬዝዳንት ተገኝተዋል፡፡
ስብሰባው የዓለምን የ1.5°C የአየር ንብረት ግብ ለማሳካት የምግብ ስርአቶችን እና የመሬት አጠቃቀምን ማሻሻል አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።
በአዘርባጃን ባኩ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ የካርበን ልቀትን መቀነስ፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ማቋቋም እና ዘላቂ ግብርናን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።
ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በመድረኩ ኢትዮጵያ የአየር ለውጥን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ሃገሪቱ ዘላቂ የሆነ ግብርና በብሔራዊ የአየር ንብረት ፖሊሲዋ ውስጥ በማቀናጀት የምግብ ዋስትናን እና የአካባቢ ጥበቃን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት መግለጻቸውንም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።