ለአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያ ተግባራዊ ምላሾች

1 Day Ago 113
ለአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያ ተግባራዊ ምላሾች

ኢትዮጵያ ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ላለው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት (GHG) ምንም አስተዋጽኦ የሌላት ቢሆንም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ከሚደርስባቸው ሀገራት አንዷ ነች፡፡

በዚህም ምክንያት ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እንቅስቃሴየነቃ ተሳትፎ የምታደርግ ከመሆኑም በላይ ችግሩን ለመቅረፍ የውስጥ አጀንዳ ቀርጻ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች፡፡

 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን (UNFCCC) ሂደቶች ላይ በተለይም በባለድርሻ አካላት ዓመታዊ ስብሰባዎች (COP) ላይ በንቃት በመሳተፍ የመፍትሔ ሀሳቦችን እያቀረበች ነው።

1.ኢትዮጵያ በዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉበኤ (COP) ላይ ያላት ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች (COP) ላይ ስትሳተፍ የአፍሪካን አጀንዳ ይዛ ነው፡፡ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምንም አስተዋጽኦ ሳታደርግ በችግሩ ግን ተጠቂ መሆኗን ነው ኢትዮጵያ የምትሞግተው፡፡ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሀገራት አፍሪካ የሚደርስባትን የአየር ንብረት ለውጥ ተተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችላትን ድጋፍ እንድታገኝ ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገች ነው፡፡

በጉባኤው በፓሪስ ስምምነት መሰረት የሙቀት መጠንን 1.5 ድግሪ ሴንቲግሬድ ላይ ለመገደብ ለጉዳት ካሳ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለካርቦን ንግድ የተገባው ቃል ተግባራዊ እንዲሆንም እየጠየቀች ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም ጉባኤው ላይ አጀንዳ ከማቅረብ አልፋ በራሷም ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ትገኛለች፡፡

ድርቅ እና በረሃማነት እያስፋፋ ያለውን የደን መጨፍጨፍን እየተከላከለች የደን ሽፋኗን ለማሻሻል እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ውጤታማ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ የካርቦን አማቂ ጋዝን ለመቀነስ እያደረገችው ባለው እንቅስቃሴ በ2022 የካርቦን ልቀትን በ64 በመቶ ለመቀነስ ግብ አስቀምጣ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ ይህ ትልቅ ግብ ለማሳካትም በታዳሽ የኃይል አቅርቦት፣ የደን ሽፋንን በመጨመር እና የመሬት አጠቃቀምን በማሻሻለ 255 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ እየሠራች ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የሚቋቋም የግብርና፣ የውሃ፣ የጤና እና በመሰረተ ልማት ዘርፎች እየሠራች ነው። በዚህም የደን ሽፋኗ በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17.2 በመቶ አሁን ወደ 23.6 በመቶ ሊያድግ የቻለ ሲሆን፣ በ2022 ይህን ሽፋን ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ እየሠራች ነው፡፡ እነዚህን ግቦች በታሰበላቸው ጊዜ ከተቻለም ቀድሞ ለማሳካት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገንዘብ፣ የቴክኒክ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ትሻለች።

  1. የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተቀመጡ ዋና ዋና ሀገራዊ ግቦች

የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ (CRGE) ስትራቴጂ አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በ2022 ዓ.ም ዝቅተኛ የካርቦን ኢኮኖሚ ለመፍጠር ያለመ ዋነኛ የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ፖሊሲ ማዕቀፍ ነው። ታዳሽ የኃይል ምንጭን ማስፋፋት እንዱ የዚህ ስትራቴጂ ማሳኪያ ነው፡፡ እንደ ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባሉት የውሃ ኃይል ማመንጫዎች እና የንፋስ፣ የፀሐይ እና የጂኦተርማል የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰች ትገኛለች። ዓላማው መቶ በመቶ ታዳሽ የኃይል ማመንጫዎችን ማግኘት እና ወደ ጎረቤት ሀገራትም ንጹህ ኃይል ምንጭ በመላክ ብክለትን መቀነስ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርና እና የዐፈር ማገገሚያ ጥረቶችን በማሳደግ የሰብል ምርትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል የሚሠራው ሥራም ሌላኛው የስትራቴጂው አካል ነወ፡፡ በተለይ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ተፅዕኖውን ለመቋቋም ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የደን መጨፍጨፍ የሚያስከትላቸው ጉዳቶችን ለመቋቋም ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል ትልቁ ሥራ ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም በተጀመረው አረንጓዴ አሻራ ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ተችሏል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የዐፈር መሸርሸርንም ሆነ የካርቦንን ልቀትን በመከላከል ዘላቂ የሆነ ጤናማ ሥነ ምህዳር ይፈጥራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአየር ንብረት መከላከል አካል የሆነው ፕሮጀክቱ የደን ሽፋንን በመጨመር እና ሥነ-ህይወታዊ ስብጥርን በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና የደን መመንጠርን በመከላከሏ ነው በስድስት ዓመታት ውስጥ የደን ሽፋኗን ከ6 በመቶ በላይ ማሳደግ የቻለችው፡፡

ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም እንዲስፋፋ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ላይ እየሠራች ነው፡፡ እነዚህ እርምጃዎች በማኅበረሰብ ደረጃ በተለይም በገጠር እና ደን ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖረውን የኅብረተሰብ ክፍል ያቀፉ ናቸው። ፕሮግራሙ የዐፈር እና የውሃ ጥበቃ፣ የዐፈር መሸርሸርን መከላከል እና ዘላቂ የግብርና ልማትን ያካትታል። እነዚህም የደን መጨፍጨፍን የሚቀንሱ እና የአካባቢውን መተዳደሪያ የሚያሻሽሉ ተግባራት ናቸው።

የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፉም ለሀገራዊ የአየር ንብረት ተፅዕኖ ቅነሳ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው፡፡ መንግሥት የኤሌክትሪክ ባቡርን በማስፋፋት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን (EVs) በማበረታታት በከተሞች ውስጥ ንጹሕ የሕዝብ ትራንስፖርት አማራጮች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ላይ ይገኛል።

  1. ፈተናዎች እና ፍላጎቶች

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በንቃት እየሠራች ቢሆንም አጀንዳዋን ውጤታማ ለማድረግ ግን ፈተናዎች አልታጡም፡፡ ከነዚህ ፈተናዎች መካከልም አንዱና ዋነኛው የፋይናንስ አቅም ውስንነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች ሀገር እንደመሆኗ መጠን ሀገራዊ የአየርን ንብረት ለውጥ ፖሊሲዋን በሙሉ አቅሟ ለመተግበር የፋይናንስ እጥረት ዋነኛ ፈተናዋ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጡን ውጤታማ ለማድረግ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ጥሪ የምታደርገውም ለዚህ ነው፡፡

ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረት ለታዳሽ ኃይል፣ ለግብርና እና ለውጤታማ የውሃ አጠቃቀም እውን መሆን የሚረዱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ይጠይቃል። እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ለማግኘት ደግሞ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ከበለጸጉ ሀገራት ጋር የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት ያስፈልጋል።

  1. የኢትዮጵያ ተስፋዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP) ተግባራዊ ምላሾች

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባዎች (COP) ላይ በርካታ ቅድሚያ ሊሰጡዋቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ማመላከቷን ቀጥላለች፡፡ ከነዚህ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች የተሻሻለ የአየር ንብረት ፋይናንስ አንዱ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ፋይናንስ ለማቅረብ የገቡትን ቃል እንዲፈፅሙ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጥሪ አድርጋለች። ይህ የገንዘብ ድጋፍ የየሀገራቱ ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ውጤታማ እንዲሆን ወሳኝ ነው በማለትም መከራከሪያ ታቀርባለች።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት አንዲበረታታም የኢትዮጵያ ጥያቄ ነው፡፡ የአፍሪካ ሀገራት ለምግብ እና ውሃ ደህንነት ወሳኝ የሆነውን የአየር ንብረት ተፅዕኖ የመቋቋም አቅምን ለመገንባት እና ማላመድ የሚያስችል በቂ የገንዘብ ድጋፍ እንዲየገኙም በጉባኤዎቹ ላይ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አቅርባለች።

የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች ጋር ተያይዞ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስወገድ በጉዳዩ ምንም አስተዋጽኦ ለሌላት አፍሪካ የጉዳት ማካካሻ እንዲደረግ ጥሪ እያቀረበች ሲሆን፣ ጉዳዩ አወዛጋቢ ሆኖ ቢቆይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ታምኖበት በሀሳብ ደረጃ በስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የዓለም ሙቀት መጨመርን 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ላይ ለመገደብ የተደረሰው የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ ኢትዮጵያ በየጉባኤው ጥሪ ማቅረቧን ቀጥላለች፡፡ አፍሪካ ያለ ጥፋቷ እየተጋፈጠች ያለውን በአየር ንብረት ለውጥ የመጣባትን ችግር እንድትቋቋም ይህ ቃል ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ኢትዮጵያ በተጨባጭ ማስረጃዎች እየተከራከረች ነው። ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎም ግን በየዓመቱ በሚደረገው የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ቃል ገብቶ ከመለያየ ያለፈ ተጨባጭ እርምጃ እየታየ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገችው ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በአፍሪካ ውስጥና በዓለም አቀፍ መድረክ የዘላቂ ልማት አርዓያ አድርጓታል። እርምጃዎቿ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከአካባቢያዊ ዘላቂነት ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማስኬድ ለሚጥሩ ሀገራት አርዓያ እንደትሆን አድረገዋታል። ይሁን እንጂ እነዚህን ግቦች በተሟላ ሁኔታ ለማሳካት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ከፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና አቅም ግንባታ ጋር በተያያዘ በዘላቂነት የሚሰጠው ድጋፍ የማያወላዳ ሆኖ ቀጥሏል። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ ምንም ይሁን ምን ግን ግፊቷንም እያጠናከረች የጀመረችውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡

በለሚ ታደሰ

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top