በዝምታ ተጀምሮ በዝምታ ለምረቃ የበቃው አስደናቂው የቤኑና መንደር

1 Mon Ago 413
በዝምታ ተጀምሮ በዝምታ ለምረቃ የበቃው አስደናቂው የቤኑና መንደር

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት ተወጥኖ በዛሬው ዕለት ለምርቃት የበቃው ቤኑና መንደር የበሰቃ ሐይቅ ድብቅ ውበትን መግለጥ ጀምሯል፡፡

ከመተሃራ ከተማ አቅራቢያ ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የቤኑና መንደር ልዩ የተፈጥሮ ገጸ በረከትን የተላበሰ ልዩና ማራኪ የመዝናኛ ስፍራ ሆኗል፡፡

ለመዝናኛ መደራሻነት ተብሎ የተገነባው የቤኑና መንደር፣ ግርማ ሞገስ ባላቸው የአዋሽና አሰቦት ብሄራዊ ፓርኮች አቅራቢያ ነው የሚገኘው፡፡

በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የተገነበው የቤኑና መንደር፣ ከአነስተኛ መንደርነት ወደ አእምሮን የሚያረጋጋ ምቹ ማረፊያነት ተቀይሮ፣ የአይበገሬነት ማሳያ ሆኗል፡፡

አሁን ላይ በለምለም አረንጎዴና በቅንጡ ቪላዎች፣ በባህላዊ ቤቶች ተውቦ እረፍትና መዝናናትን ለሚሹ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል፡፡

የቤኑና መንደር በግንባታዎቹ ባህላዊና ዘመናዊ የኪነ ህንጸ ጥበቦችን ተላብሷል፡፡

ረጋ ብሎ የሚነፍሰው ንፋስ፣ ከአካባቢው የሚወጡ የተፈጥሮ ድምጾች፣ ከውኃ ላይ የሚነሰው ነፋሻማ አየር ውስጣዊ መንፈስን ያረጋጋል፡፡

ለጀብደኞች የማይረሳ ጊዜያትን የሚያሳልፉበት፣ ልዩ የማደሪያ ቦታ፣ 5 ተንቀሳቃሽ የመኪና ቤቶችን በውሰጡ ይዟል፡፡

እንግዶች በአገልግል ሬስቶራንት ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የምግብ ዓይነቶችን እየተመገቡ፣ በአቅራቢያቸው ባለው የውኃ ፏፏቴ ድምጽ ታጅበው ማለዳቸውን የሚጀምሩበት ስፍራም ተበጅቶለታል፡፡

ከፍታ ላይ የተገነቡት ተንሸራታች ጣሪያዎች፣ በልዩ የጥበብ ማስጌጫዎች ተሽቆጥቁጠው ልብን የሚሰውር እይታዎችን የስኮሞኩማሉ፡፡

በውብ ቅርጻ ቅርጻ የተዋቡ ግርግዳዎች የሀገር ውስጥ የእደ ጥበብ ባለሙያዎችን ድንቅ ችሎታ ያሳያሉ፡፡

የኢትዮጵያን ባህላዊ የቡና አፈላል ስርዓት የሚቀርብበት፣ በመጂልስ የተዋበ ባህላዊ ቅርጽን ይዞ የተሰራው ማራኪ ቤት ለመንደሩ ልዩ ገጽታን አለብሶታል፡፡

ምሽት ላይ ክዋክብት ስር ሆነው ሙዚቃ፣ ዳንስና ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን የያዙ ጥበባዊና ባህላዊ ትእይንቶችን በአምፊ ቲያትር ይታደማሉ፡፡

መንደሩ በምሽት የማይረሳ ውብ ግዜን ለማሳለፍና ነፍስን ለማደስ በሚሆን መልኩ እንዲሆን ተደርጎ ተሰርቷል፡፡

አካልንና መንፈስን ለማደስ የመዝናኛ ጋሪ፣ ብስክሌት፣ የእግር ኳስ መጫዎቻ ሜዳ፣ የቴንስና መሰል የመዝናኛ ስፍራዎች ውብ በሆነ መልኩ ተገንብተዋል፡፡

እንግዶች ወደ መንደሩ ጎራ ሲሉ 10 ሄክታር በሚሸፍነው ለም መሬት ላይ የሚገኙትን  ላሞች፣ ግመሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች መጎብኘት የሚችሉበት ሁኔታ የተመቻቸ ነው፡፡

በከፊል ደረቃማ መልካአ ምድሩና የበለጸገ ብዘኃ ህይወቱ የሚታወቀው የአሰቦት ብሄራዊ ፓርክ የተለያዩ አእዋፍት ዝርያዎችን፣ ዝንጀሮና ከርከሮ ያሉ የዱር እንስሳት በውስጡ ይገኛሉ፡፡

የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ በአንጻሩ በአስደናቂ መልክዓ ምድራዊ ገጽታው የሚታወቅ ሲሆን የአዋሽ ወንዝ ሸለቆ፣ የተፈጥሮ ፍል ውኃዎች፣ በእሳተ ጎሞራ የተፈጠሩ የመሬት ገጽታዎች የታደለ ነው፡፡

የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ የበረሃ አጋዘን፣ የሜዳ ፍየልና ከ450 በላይ የአእዋፍት ዝሪያዎች መገኛ ነው፡፡

በእነዝህ ዋና ዋና የቱሪስት መስህቦች አቅራቢያ የተገነባው የቤኑና መንደር ስትራቴጂካዊ የመዝናኛና የኢኮቱሪዝም ተፈጥሮን አጣምሮ ያያዘ፣ ተሞክሮ የመሆን እምቅ አቅም ያለው ነው፡፡

በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ፍላጎትን በአጅጉ እንደሚደግፍም ይጠበቃል፡፡

በመሃመድ ፊጣሞ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top