ዶናልድ ትራምፕ 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ

2 Mons Ago 462
ዶናልድ ትራምፕ 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ
በአሜሪካ እጅግ ጠንካራ ፉክክር በታየበት 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ 279 ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡
 
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ለ2ኛ ጊዜ አሜሪካንን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ለመምራት የሚያስችላቸውን ድምፅ አግኝተዋል፡፡
 
የአሁኗ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ዴሞክራት ፓርቲን በመወከል በታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
 
በአውሮፓውያኑ 2024 በዓለም ከተካሄዱና ከሚካሄዱ ሀገራዊ ምርጫዎች መካከል የዓለምን ትኩረት የሳበ፣ ከአሜሪካ አልፎ በዓለም ፖለቲካ ትልቅ ትርጉም የሚኖረውን 47ኛውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ አሸንፈዋል፡፡
 
በአሜሪካ ድምፅ መስጠት ከሚችሉ 240 ሚሊዮን ዜጎች መካከል 161 ሚሊዮን መራጮች ድምፅ ለመስጠት ካርድ ወስደዋል።
 
ከምርጫው በፊት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ በአሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ሚቻጋን፣ ኔቫዳ፣ ሰሜን ካሮላይና፣ ፔንሰልቫኒያ እና ዊስኮንሲን 7 ግዛቶች ሁለቱም ፓርቲዎች እኩል የመራጮች ድጋፍ ያላቸው በመሆኑና ከዚህ ቀደም ተፈራርቀው ስላሸነፉ አሁንም ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ሲገለፅ ቆይቷል።
 
ይሁን እንጂ ዶናልድ ትራምፕ በ7ቱም ግዛቶች ተቀናቃኛቸውን ካማላ ሃሪስን በማሸነፍ ታሪካዊ ድል አስመዝግበዋል።
 
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በታሪኳ ትልቅ ኢኮኖሚ እንዲኖራት፣ ለአሜሪካ ሰራተኞች ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ በዓለም በኃይል አቅርቦት በሌሎች የተያዘውን የበላይነትን ለማስተካከል፣ የአሜሪካን ብሔራዊ ደህንነትና ድንበር ለማስጠበቅ፣ በአደንዛዥ እፅ እና ወንጀልን ለመቀነስ ቃል የገቡት ትራምፕ የአሜሪካውያንን ልብ አግኝተው ዳግም 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተምርጠዋል፡፡
 
የትራምፕ ደጋፊዎች ፕሬዚዳንቱ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል፣ በመመካከለኛው ምስራቅ ያለው ጦርነት እንዲቆም፣ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ባለው ጦርነት ላለመሳተፍ የገቡትን ቃል እንያዲከብሩ መጠየቅ ጀምረዋል፡፡
 
በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top