ዴንማርክ ለኢትዮጵያ ብልፅግና የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የዴንማርክ ልዕልት ቤንዲክት አስትራይድን አስታወቁ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤የዴንማርክ ልዕልት ቤንዲክት አስትራይድን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት ዴንማርክ የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆኗን አንስተው፤ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በኢኮኖሚው መስክ የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
ዴንማርክ በተለያዩ መስኮች እያደረገች ላለው ድጋፍም ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ልዕልት ቤንዲክት አስትራይድን በበኩላቸው፤ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች እያካሄደች ያለውን የልማት ስራ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ሀገራቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።