የጥምቀት የአደባባይ በዓል በኢትዮጵያ በጥር ወር ከሚከናወኑ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ሲሆን በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ከጥር 10 ጀምሮ የሚከናወን ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓት ነው፡፡
የበዓሉ አከባበር ከዋናው የሀይማኖት መሰረታዊ ትርጉም ባሻገር በዓሉ ለሰው ልጆች ባህል፣ ኪነ ጥበብ፣ ስነ ጥበብ ማደግ ተፋቅሮና ተከባብሮ መኖር፣ ለቱሪስት መዳረሻነት፤ ለገጽታ ግንባነት ታላቅ ጠቀሜታን አበርክቷል እያበረከተም ይገኛል።
የጥምቀት በዓል በመላው ኢትዮጵያ የቤተ-ክርስቲያኗ ዶግማ ቀኖናና ትውፊት መሰረት አድርጎ እንደ የአካባቢው ባህልና ቋንቋ ሁኔታ ይከበራል። በተለይ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ፣ በጎንደር አጼ ፋሲል መዋኛ፣ በአክሱም ማይሹም፣ በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ዩሐንስ አምባ ገጠርጌ ባህረ ጥምቀት፣ በባቱ ሀይቅ ላይ፣ በኢራንቡቲ፣ በከፍተኛ ድምቀት ይከበራል፡፡
የጥምቀት በዓል ቱርፋቶች
ብሔር፣ ባህል ቋንቋ ሳይለያይ በአንድ የሚከበር መሆኑ፤
በባዕሉ የወግ፣ የባህል አልባሳት፣ የእጅ ስራ ጥበባት የሚታዩበት ኢትዮጵያዊ ስንኝ፣ ግጥም ዜማ የሚማሩበት፣ የሚነገሩበት ትሩፋት መሆኑ፤
ሥርዓተ ወጉ ሳይፈልስ ወጣቱ ባህሉን፣ እምነቱን ወጉንና ክብሩን ተብቆ አስጠብቆ መቆየቱ፤
በየጊዜው በዓሉ መደብዘዝ ሳይታይበት እየደመቀ እየፈካ መከበሩ፤
የአገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚ ቀልብና አይን መማረኩ፤
ጎብኚዎች የኢትዮጵያን የባህል አልባሳት፣ ሙዚቃ፣ አመጋገብን ጨምሮ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ወጎችን መጎብኘት እንዲችሉ እድል ይሰጣል።
የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን እንቅስቃሴ ላይ በጎ አስተዋፅኦ በማበርከት ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል።
ጥምቀት ሃይማኖታዊ በዓል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ማሳያ ነው፡፡ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን የመሳብ ችሎታው ለአገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ወሳኝ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
በመሆኑም ጥምቀትን እና መሰል የማይዳሰሱ የአደባባይ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ በዓላትን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እና ሁሉም ሚዲያዎች በሚገባ በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ በቱሪዝም መዳረሻነት ስም በማጠናከር በታለመለት ጊዜ እውን ማድረግ ይችላል።
ሚኒስቴር መሥሪያቤታችንም የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በልዩ ሁኔታ በሚታደሙባቸው ጎንደር፣ ባቱ እና ኢራንቡቲ ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እና ከአማራ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የሚያከብር ሲሆን በዚህና በመሰል በዓላት ሕብረተሰባችን እና ሚዲያዎቻችን ልዩ ትዝታ ቀስቃሽ ምስሎችን በማስቀረት በየማህበራዊ ገጾቻቸው በልዩ ልዩ ሀገራዊ እና የውጭ ቋንቋዎች ምስሎቹን በማጋራት በጋራ የመስህብ ሀብቶቻችንን እንድናስተዋውቅ ይጋብዛል።
ቱሪዝም ሚኒስቴር