ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶቻችን ኢትዮጵያ ለጀመረችው ምክክር ውበትም ጉልበትም ናቸው ሲሉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ፡፡
በዛሬው የኢቲቪ አዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" ዝግጅት ሀሳባቸውን ያጋሩት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሪዎች፤ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች ኢትዮጵያ ለጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ያላቸውን አስተዋፅኦ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አንድን ሀገር ለማዳንም ሆነ ስም እና ክብሯን አስጠብቆ ለመቀጠል ምክክር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ጫፍ እና ጫፍ የረገጡ ትርክቶች በስፋት ይነገራሉ የሚሉት ጠቅላይ ፀሐፊው፤ በዚህም አብዛኛውን ጊዜ ለግጭት መንስኤ ሲሆኑ እንደሚስተዋሉ ነው የሚያነሱት።
"ግጭት የፈጠረ፣ የተጣላ እንዲሁም የተኳረፈ ሲኖር ሽማግሌ ገብቶ የማስታረቅ ባሕል አለን" ያሉት ቀሲስ ታጋይ፤ ይህም ከሃይማኖታዊ እሴቶች እንደሚመነጭ እንደሆነ ነው ያመላከቱት፡፡
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አካታች እና አሳታፊ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
በመነጋገር እንጂ በጦርነት ችግር አይፈታም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች እና ልዩነቶች ላይ መምከር እና መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ሁሉም ነገር ላይ አንድ አቋም መያዝ አይቻልም፤ ነገር ግን በምክክር መቀራረብ ይቻላል ያሉ ሲሆን፣ እኔ ብቻ ነኝ ልክ የሚለው ሀሳብ ሀገር ያፈርሳል ብለዋል፡፡
በሁሉም ክልሎች የምክክር አጀንዳ ልየታው እንደተካሄደ ገልጸው፤ በቀሩት የአማራ እና ትግራይ ክልሎችም አስቻይ ሁኔታ ሲፈጠር እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
የሀገር ግንባታ የሚታየው በአዲስ ዕይታ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ደግሞ ሀገራዊ ምክክሩ የእውነት ፍለጋ ሂደት ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡
በሌሎች ሀገራት የምክክር ሂደት ልዩነቶችን ወደ አንድ ጠረጴዛ በማምጣት የማቀራረብ እና የዘመናት ቁርሾን የመሻር ስራዎች ተሰርተው ውጤት ማምጣት ተችሏል ብለዋል፡፡
በሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን ለማሻገር መንገድ ተጀምሯል፤ በዚህም የኢትዮጵያን ችግር መቅረፍ ይቻላል ነው ያሉት።