የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በጋራ ሊሰሩባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አጠቃላይ አሰራርን ጎብኝተዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ አርአያስላሴ በዚሁ ወቅት፤ የብሄራዊ መታወቂያ ተደራሽነቱ እንዲሰፋ እና ጠቀሜታውን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ኢቢሲ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ብሄራዊ መታወቂያ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ የሀገሪቱ ሀብት እንዳይባክን እና የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶች እንዳይኖሩ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡
ብሄራዊ መታወቂያ የሰዎችን ማንነት የሚለይ በመሆኑ በሀገሪቱ የሚከሰቱ ወንጀሎች እንዲቀንሱ ያስችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ በአፍሪካ ደረጃ ብሄራዊ መታወቂያን ተደራሽ በማድረግ ሰፊ ስራ እየሰራች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።
ኢቢሲ እያደረገ ስለለው እገዛ ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚ ነብዩ ባዬ በበኩላቸው፤ ይህ ዘመናዊ እና ቀልጣፍ አሰራር ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ተናግረዋል።
ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አሁን ላይ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተመልክቻለው ያሉት ምክትል ስራ አስፈፃሚው፤ ተቋሙ በእድገት ላይ ሆኖ በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ብሔራዊ መታወቂያ በሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ኢቢሲ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
በሜሮን ንብረት