ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

11 Mons Ago
ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር እና የፓኪስታን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተፈራርመዋል።

በፓኪስታን መዲና ኢዝላማባድ በተከናወነው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በመስኩ ያላቸውን ተሞክሮ የሚለዋወጡበት እና አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ነው።

ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራት የሳይንስ እና የፈጠራ ተቋማት አብረው የሚሠሩበትን መደላድል እንደሚፈጥር የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፎዚያ አሚን ገልጸዋል።

ከስምምነቱ ዐቢይ ትኩረቶች አንዱ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የኢንዱስትሪዎች ትሥሥርን ለማጎልበት የሚሠሩ ሥራዎችን ማሳደግ እንደሆነም ገልጸዋል።

ፓኪስታን ይበልጥ በጨርቃጨርቅ እና ፈርማሲውቲካል ዘርፎች ከፈጠረችው አቅም ኢትዮጵያ ልምድ የምትቀስምበትን ዕድል ስምምነቱ እንደሚፈጥርም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጨምረው ገልጸዋል።

የፓኪስታን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዋና አማካሪ ዘይኑል አበዲን በበኩላቸው፣ ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል አዲስ የትብብር መስክ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ሀገራቱ በሳይንስ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ የፈጠሩትን አቅም እንዲያጎለብቱ እና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አፈፃፀም ለመግባት ሚኒስቴሩ ቁርጠኛ ዝግጅት ማድረጉም ተገልጿል።

የስምምነቱ ዝርዝር የአፈፃፀም የጋራ ዕቅድ እንደሚዘጋጅም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top