የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያሏትን አቋሞች ይበልጥ ያንጸባረቀችበት ነው፦ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

23 Hrs Ago 79
የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያሏትን አቋሞች ይበልጥ ያንጸባረቀችበት ነው፦ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ያሏትን አቋሞች ይበልጥ ያንጸባረቀችበት እንደነበር የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
 
ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ የነበራትን ተሳትፎ እና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 
በጉባኤው የተንጸባረቁ ሀሳቦች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች የሚያሳኩ ሆነው መገኘታቸውን ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ተናግረዋል።
 
ጉባኤው የአባል ሀገራቱ ፍላጎቶች፣ጥቅሞች እና አቋሞች የተጸባረቁበት እና የተበታተኑ ድምፆች ወደ አንድ የመጡበት እንደነበር ገልጸዋል።
 
በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዳጊ ሀገሮች ድምጻቸው የሚሰማበት፣ ኢ-ፍትሀዊ የሆነው የፋይናስ አቅርቦት፣ በጸጥታው ምክር ቤት ያለው ኢ-ፍትሃዊ ውክልና እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለውጥ ለማድረግ የጋራ ፍላጎቶች የታዩበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ እና የባለ ብዙ ወገን የግነኙነት መድረኮች ማካሄዳቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
 
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርኋ ከታሪክ፣ ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ፣ ከህዝብ ብዛቷ እንዲሁም ከኢኮኖሚ እድገቷ ጋር የሚመጥን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷንና አቋሟን ማንጸባረቃቸውን አንስተዋል።
 
"በምግብ ዋስትና እራስን ለመቻል በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ በተለይም በስንዴ ዘርፍ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ሰፊ የስንዴ ምርት እንዲኖር እያደረገች ያለውን ጥረት እና ያስገኘውን ውጤት ለማስረዳት እድል አግኝታለች" ብለዋል ፡፡
 
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ኢትዮጵያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ 40 ቢሊዮን ችግኖችን በመትከል እያካሄደች ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ ሌሎች ሀገራትም በተሞክሮነት የሚወስዱት መሆኑን በመድረኩ መጠቀሱን አመላክተዋል፡፡
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top