አካታች የዓለም ሥርዓትን ለመፍጠር የብሪክስ ሚና

1 Day Ago 171
አካታች የዓለም ሥርዓትን ለመፍጠር የብሪክስ ሚና

በብራዚል፣ሩሲያ፣ሕንድ፣ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ጥምረት የተጀመረው ብሪክስ ሌላኛው የዓለም ባለብዙ የዲፕሎማሲ መድረክ እየሆነ ነው። በተለይ የአሜሪካ፣የካናዳ፣ የጃፓን፣የጀርመን፣የዩናይትድ ኪንግደም፣የፈረንሳይ እና የጣሊያን ጥምረት የሆነው ቡድን ሰባት (G7) በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ተፅዕኖ በመቀነስ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለማስፈን ያለመም ነው።

ብሪክስ ሁሉን አቀፍ ጥምረት ለመሆን እያደረገ ባለው ጥረት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶችን በአዲስ በአባልነት በመያዝ አባላቱን ወደ 10 አሳድጓል፡፡ የእነዚህ አዳዲስ ሀገራት በአባልነት መካተት ለጥምረቱ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ይጨምራል።

በተለይም  ነዳጅ አምራቾች ከሆኑት ሀገራት መካከል ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ብሪክስን መቀላቀላቸው ቡድኑ በኢኮኖሚው ረገድ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ይጨምራል። በደቡብ-ደቡብ ትብብር አማካኝነት በጥቂት የምዕራቡ ዓለም ሀገራት የተያዘውን የኢኮኖሚ ሥርዓት የበላይነት ሚዛናዊ ለማድረግ እየሠራም ይገኛል፡፡

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እንደ አይ ኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክ ባሉት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የበለጠ ድምጽ እንዲኖራቸው ግፊት እያደረገ ያለጥምረትም ነው፡፡ ብሪክስ በቡድን 7 እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ከሚደገፉ የፋይናንስ ተቋማት የማይገኙ ድጋፎችን ለማመቻቸት የራሱ የሆነ የልማት ባንክም አቋቁሟል፡፡ ባንኩ ለብሪክስ አባል ሀገራት እና ከዚያ ባሻገር ላሉት አዳጊ ሀገራት ለዘላቂ ዕድገት የሚረዱ የልማት ፕሮጀክቶችን ይደግፋል፡፡ 

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት የህንድ እና የቻይና የመግዛት አቅም ከአጠቃላይ የቡድን 7 ሀገራት ልቋል፡፡ የብሪክስ ሀገራት ከ32 እስከ 40 አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ይህም የቡድን 7 ሀገራት የመግዛት አቅም ድርሻ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ  ይገለጸል፡፡ ከ40 በመቶ በላይ የዓለም ሕዝብ ቁጥርን የያዘው ብሪክስ ለዚህ የጥምረቱ የመግዛት አቅምን የሚጨምር ነው፡፡

እንደ ሩሲያ እና ቻይና ያሉ የጥምረቱ አባላት በየራሳቸው ገንዘብ መገበያየት ላይ ማተኮራቸው እና ግብይቱንም ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ብሪክስ

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2023 በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ ጉበኤ ነው ብሪክስን እንድትቀላቀል የተወሰነው፡፡ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ ሙሉ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ባላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ ባላት ሚና ጥምረቱን መቀላቀሏ ትርጉን ያለው ለውጥ የሚያመጣ ይሆናል። በአህጉሪቱ ሁለተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት እና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ካሉት ሀገራት አንዷ መሆኗም የጥምረቱን ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የምትገኝ እና በአፍሪካ ዋነኛ የኢኮኖሚ ማዕከል ለመሆን እየሠራች ያለች ሀገር ነች። የብሪክስ አባልነቷ ከሌሎች የብሪክስ አባላት ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የሚያጎለብት ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሺቲቭ ያሉ የመንገድ፣ የባቡር እና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ባካተተው ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታ አካል ነች፡፡ የብሪክሱ አዲስ ልማት ባንክ (NDB) ኢትዮጵያ የዕድገት ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ የማግኘት ዕድሏን የሚጨምር ሌላ አቅም ይሆናታል። ይህም በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ መሪ ሆና እንድትቀጥል የሚያግዛት እንደሚሆን በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚያደርጉ አካላት ይገልጻሉ።

የአፍሪካ ኅብረት መሥራች እና መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ በብሪክስ እና የአፍሪካ አህጉር መካከል ድልድይ ሆና የምታገለግልም ነች። ይህ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና አፍሪካ ላይ ያላት ተፅዕኖ አባል የሆነችበት ብሪክስ የምዕራባውያኑ የፋይናንስ ተቋማት ፍትሃዊ እንዲሆኑ የጀመረውን ጥረትን የሚያግዝም ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ለደቡብ-ደቡብ ትብብር መሰረት የሚሆነውን የገለልተኝነት አቋም በመያዝ የምትታወቅ ሀገር ነች። ይህም የኢትዮጵያ አቋም ባለ ብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓትን ለመፍጠር እየሠራው ካለው የብሪክስ አቋም ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዕዳ ማቅለል እና ፍትሐዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ጉዳዮች ላይ፣ እንደ ተመድ ባሉ የብዙ ወገን ፎረሞች ሁሉን አቀፍ እንዲሆኑ ላላት አቋም ተጨማሪ አቅም ሊሆን ይችላል።

ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ በአባልነት መቀበሉ እንደ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) በመሳሰሉ የአህጉራዊ የልማት ስትራቴጂዎች ላይ ያለውን ቅንጅት ይጨምራል። በፓን አፍሪካኒዝም የማይደራደሩት ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉት ሀገራት የጥምረቱ አካል መሆናቸው ደግሞ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የመደራደር አቅም ሊያጎለብት ይችላል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ዋነኛ የአፍሪካ የኃይል ምንጭ ለመሆን እየሠራች ነው። የብሪክስ አባልነቷ ደግሞ በኢነርጂ ዘርፍ፣ በቴክኖሎጂ ልውውጥ እና በኢንቨስትመንት ረገድ እያሳየችው ያለውን ዕድገት የሚያጎለብት ነው። ይህም በቀጣናው የኃይል ማዕከል ለመሆን እያደረገች ያለውን ጥረቷን የሚያግዝም ነው። 

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top