ለሴቶች እፎይታን የፈጠረው…

1 Day Ago 55
ለሴቶች እፎይታን የፈጠረው…
ከአዲስ አበባ 47 ኪ.ሜ ወደምትርቀው ቢሾፍቱ ተጉዘን የ32 ዓመቷ ወ/ሮ አይንዓለም ሞላን እናስተዋውቃችሁ፡፡
 
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ አይንዓለም፣ አንድ ለትምህርት ያልደረሰች የ1ዓመት ከ5 ወር ሕጻን እንዲሁም ሁለት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ልጆች አሏት።
 
የትዳር አጋሯ ስራ በመፍታቱ ምክንያት የቤተሰቡ ችግር ላይ መውደቅ ያሳሰባት ወ/ሮ አይንዓለም፣ የቤቱን ቀዳዳ ለመሙላት የጉልበት ስራ እስከመስራት እንደደረሰች ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች፡፡
 
የጉልበት ስራው አድካሚ እና እንደምትፈልገው ያልሆነላት ወ/ሮ አይንዓለም፣ ስራውን ለመተው እያሰበች በነበረበት ወቅት በጀርመን የተራድኦ ድርጅት ውስጥ ስራ ለመጀመር የሚያስችል ስልጠና መኖሩን ትሰማለች።
 
"ስራ ከሆነ ምንም ዋጋ እከፍላለው" የምትለው ወ/ሮ አይንዓለም ስልጠናውን ሕጻን ልጇን እያዘለች አልፎ አልፎም የሚጠብቅላት ሰው ጋር እያስቀመጠች ተከታትላ መጨረሷን ተናግራለች፡፡
 
በሰለጠነችው ስልጠና መሰረትም በድርጅቱ ውስጥ ተቀጥራ ከ4 እስከ 5 ወር የሚቆይ እና የሚታጠብ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) በማምረት ላይ እንደምትገኝ ገላጻለች።
 
በዚህም አሁን ላይ በቀን ከ20 ፍሬ በላይ የሚሆኑ የንጽሕና መጠበቂያዎችን እየሰራች እንደሆነ ተናግራለች።
 
በገጠሩም ሆነ በከተማ አካባቢ የሚኖሩ የንጽህና መጠበቂያ ለመግዛት አቅም የሌላቸው አንዳንድ ሴቶች፣ይህን የሚታጠብ እና መልሶ አገልግሎት ላይ የሚውለውን ሞዴስ በዝቅተኛ ዋጋ ማግኘት እንዲችሉ ይረዳቸዋል ብላለች።
 
አንድም ሴት የንጽህና መጠበቂያ በማጣት ምክንያት ከትምህርትም ሆነ ከስራ ገበታዋ እንዳትቀር ዓላማ ያደረገ ስራ ስለመሆኑም ነው የጠቀሰችው፡፡
 
ኑሮዋን በሆሳዕና ያደረገችው ሌላኛዋ የዚህ እድል ተጠቃሚ ወጣት ማርሸት ፈቃዱ፤ ከአንድ ዓመት በላይ በተቋሙ መስራቷን ትናገራለች ።
 
ወጣት ማርሸት ለራሷ የስራ ዕድል ከማግኘቷ ባለፈ፤ ይህ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ አቅም ለሌላቸው በርካታ ሴቶች እፎይታን የፈጠረ መሆኑን ትገልጻለች፡፡
 
የጀርመን የተራድኦ ድርጅቱ ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ከ25 ዓመት በላይ በዚህ እና ተመሳሳይ የሥራ መስኮች ላይ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ የንጽሕና መጠበቂያውን መግዛት ለማይችሉ ሴቶችም በነጻ እያቀረበ መሆኑ ተጠቁሟል።
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top