በአማራ ክልል በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቷል - አቶ አረጋ ከበደ

4 Hrs Ago 25
በአማራ ክልል በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቷል - አቶ አረጋ ከበደ

በአማራ ክልል በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ለዘርፉ  እድገት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

የክልሉ ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ፤ የኢንዱስትሪና ኮንስትራክሽን ዘርፉ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች እድገት መሰረት በመሆኑ ለዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የሚካሄዱ የኮንስትራክሽንና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በእውቀት ላይ ተመስርቶ በመምራት መንግስትና ህዝብ የሚፈልጉትን ልማት ለማረጋገጥ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

በክልሉ በሚገኙ ከተሞች 684 የተለያዩ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ሆኖ መጓተት፣ የጥራት ጉድለትና ሌሎች ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው አመልክተዋል።

ችግሮቹን በተቀናጀ አግባብ መፍታት እንደሚገባ የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ በመድረኩ በሚነሱ ሃሳቦች፣ ጥያቄዎችና ችግሮች ላይ በመስራት በቀጣይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አስተባባሪና የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች  ብዛት ያላቸው የመሰረተ ልማትና የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮንስትራክሽን ዘርፉ የስራ እድል በመፍጠር፣ የገበያ ትስስር በማጎልበት፣በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ዘላቂ የህዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥና ሌሎች ጥቅሞችን በማስገኘት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥም በአሰሪ ተቋማት፣ በተቋራጮችና አማካሪዎች የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት  የተሳለጠ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመድረኩ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች፣ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top