አዲስ አበባ እና የቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ የእህትማማች ስምምነት ለመፈራረም ተስማሙ

10 Mons Ago 522
አዲስ አበባ እና የቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ የእህትማማች ስምምነት ለመፈራረም ተስማሙ

አዲስ አበባ እና የቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ የእህትማማች ስምምነት ለመፈራረም መስማማታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በቻይና አስደናቂ እና ፈጣን ዕድገት ባስመዘገቡ ከተሞች የተሳካ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኙ ከንቲባዋ ገልጸዋል።

በሻንጋይ ጉብኝታቸውም ከከተማዋ ከንቲባ ጎንግ ዜንግ ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ ከተሞች የእህትማማች ስምምነት በመፈራረም እና ግንኙነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ሽግግር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

የሻንጋይ ከተማን የትራንስፖርት ማኔጅመንት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የሙዚየም አገልግሎት፣ የቆሻሻ አስተዳደር ማዕከልን እና የሎጂስቲክ አገልግሎቷን መጎብኘታቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

በጉብኝቱ ለሀገራችን ከተሞች የሚጠቅሙ ሐሳቦችን እና ልምዶችን ማግኘታቸውን ገልጸው፤ “በተለይም አዲስ አበባን ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌት በማድረግ እና የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት አቅም በመፍጠር እያስመዘገብን ያለነውን ለውጥ ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው” ብለዋል።

“ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከከተሞቻችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነች ከተማ ለማድረግ በገባነው ቃል መሠረት በላቀ ትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን!” ሲሉም አክለዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top