የኩታ ገጠም እርሻ መሰረታዊ እሳቤ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርትን ገበያ ተኮር ማድረግ ነው፡- የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም

2 Hrs Ago 11
የኩታ ገጠም እርሻ መሰረታዊ እሳቤ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርትን ገበያ ተኮር ማድረግ ነው፡- የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም
የኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ መሰረታዊ እሳቤ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን የአርሶ አደሩን ሕይወት በመቀየር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፤ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ገበያ ተኮር ማድረግ መሆኑን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም ገልጿል።
 
የተቋሙ የግብርና ኮሜርሻል ሜካናይዜሽን ክላስተር ሲኒየር ዳይሬክተር ዳኛቸው ሉሌ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራችው ቆይታ፤ የኩታ ገጠም እርሻ አርሶ አደሮች ያላቸውን የተበጣጠሰ መሬት አቀናጅተው እንዲያርሱ ያግዛቸዋል ብለዋል።
 
ይህም ለምርታማነትና ገበያ ትስስር የሚኖረው ድርሻ የላቀ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
 
ግብርና በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ውጤት ማምጣት አልቻለም ይላሉ ሲኒየር ዳይሬክተሩ።
 
ለምርት መጨመር ዋነኛው ምክንያት የግብዓት አጠቃቀም መሆኑን በማመላከት፤ የኩታ ገጠም እርሻ አርሶ አደሮች አስፈላጊውን የግብርና ግብዓቶች እና የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ስለሚያደርግ ለምርት መጨመር የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
 
ኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ ለትራክተርና ኮምባይነር እንዲሁም ለሌሎች ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀምም ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ነው ያስረዱት።
 
ይህ ዘዴ አርሶ አደሮች የእርሻ ስራውን በተመሳሳይ ጊዜ እንዲያከናውኑ እና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ያግዛቸዋል ነው ያሉት።
 
ለአብነትም ሞጆ አከባቢ የተመረተው አቮካዶ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ጠቅሰው፤ ወደ አውሮፓ ሀገራት ኤክስፖርት መደረግ መጀመሩንም ሲኒየር ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
 
ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተከተለች ያለው የግብርና ዘዴ ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ አዋጭ ስለመሆኑ ነው የገለጹት።
 
ግብርናውን በዝናብ ላይ ብቻ እንዳይመረኮዝ በማድረግ እና የመስኖ ስራዎችን በማስፋፋት የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
 
አርሶ አደሮች የወቅቱን የአየር ሁኔታ በሚመለከት፣ የአስተራረስ ዘዴን እና ለሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሚያገኙበት 8121 ነጻ የስልክ መስመር መዘርጋቱንም ዳኛቸው ሉሌ (ዶ/ር) አስታውሰዋል።
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top