በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ጋር ፍሬ ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ የተደረገው በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ነው፡፡
ውይይቱ በቡድን 20 የእዳ ማቅለያ ማዕቀፍ አማካኝነት የኢትዮጵያ የእዳ አስተዳደር የሚገኝበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ልዑክ ለአበዳሪዎቹ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባትን ለመፍታት እያደረጋቸው ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።
ማሻሻያው መርህን የተከተለ የእዳ አስተዳደር እና ሁሉን አቀፍ እድገት ማምጣትን ያካተተ መሆኑ መገለፁን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው የኢትዮጵያን የእዳ አስተዳደር አስመልክቶ የሚደረጉ ድርድሮች በተቀመጠላቸው ጊዜ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ውይይቶች ለማድረግ መስማማታቸው ተጠቁሟል።