ከፍተኛ የሆነ የወባ በሽታ ስርጭት እስከ ታህሳሥ ወር ድረስ ሊኖር እንደሚችል የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በተያዘው ዓመት በሦስት ወር ውስጥ ብቻ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡
የዝናብ ወቅትን ተከትሎ ከመስከረም እስከ ታህሳሥ ወር ባለው ወቅት የወባ በሽታ ስርጭት ከፍተኛ እንደሚሆን ነው ዶ/ር ሕይወት የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ የወባ በሽታ ሥርጭት ካሉባቸው ሀገሮች መካከል እንደምትጠቀስ ገልጸው፤ ይህንን ለመከላከል ከ8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የትንኝ ንክሻን ቅድመ መከላከል ስራ እንደተከናወነ ጠቅሰዋል፡፡
የወባ በሽታ መንስኤ የወባ ትንኝ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ሕይወት፣ በውኃ የታቆሩ ጉድጓዶች ለወባ ትንኝ ስርጭት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡
በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ክልሎች የወባ በሽታ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ የሚታይባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው አካባቢዎች ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከቦታ አቀማመጥ ጋር በተያያዘ እንደሚከሰት ጠቁመዋል፡፡
በደቡብ አካባቢ ከታቆረ ውኃ በዘለለ በእንሰት ተክል ውስጥ የሚገኝ ውኃ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ነው ያነሱት፡፡
የመተላለፊያ ወቅቶች ከመጀመራቸው በፊት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እንደሚከናወኑ የገለጹት ዶ/ር ሕይወት፤ በመኖሪያ ቤቶች እና አካባቢዎች በውኃ የታቆሩ ጉድጓዶችን እና አጋላጭ ቦታዎችን ማጽዳት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
ለወባ ትንኝ ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ አካባቢዎች የመኝታ አጎበር እንደተሰራጨ ገልጸው፤ የጸረ-ወባ ትንኝ መድኃኒት እርጭት መከናወኑንም አመላክተዋል፡፡
ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ያለባቸው ቦታዎች ላይ የጤና ኤክስቴንሽን ስራዎች በስፋት እየተሰሩ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡