የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነው፦ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ

11 Mons Ago
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነው፦ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ ታኅሣሥ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ኮሚሽነሮችም ተሹመውለት ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ሥራዎችን በምዕራፍ ከፋፍሎ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ መግለጻቸው ይታወሳል።

በሂደቱ በእያንዳንዱ ወረዳ ዘጠኝ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት እንደሚኖሩ ጠቅሰው እያንዳንዳቸው 50 ተወካዮቻቸውን የሚመርጡ መሆኑንም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።

በሂደቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱንም ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ለሚፈጠሩ ችግሮች መቋጫ ለማበጀት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር መብራቱ በየትኛውም መልኩ እገዛ እና ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የጋራ ምክር ቤቱ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ስለመዘጋጀቱም አረጋግጠዋል።

በአገራዊ የምክክር ሂደቱ እንደ አገር እየፈተኑ ያሉ ዋና ዋና ችግሮችን በመለየት መነጋገር እና የጋራ መፍትሔ ማበጀት እንዲሁም ምክክሩ እንዲሳካ ማገዝ የሁሉም ኃላፊነት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን ኅልውና አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማናቸውንም ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ለመከላከል እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጋራ ጥረታችን ሊታከልበት ይገባልም ነው ያሉት።

በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዚህ ቁርጠኛ በመሆን ሊሠሩ ይገባል ያሉት ዶክተር መብራቱ፤ የጋራ ምክር ቤቱም የሚጠበቅትን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top