በሶማሌ ክልል በሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ ልየታ ላይ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ተጠየቀ

11 Mons Ago 325
በሶማሌ ክልል በሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ ልየታ ላይ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል በሚካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ ላይ የሚሳተፉ ተባባሪ አካላት የስልጠና መድረክ ዛሬ በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ መስጠት ጀምሯል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር የስልጠና መድረኩ ያስፈለገው ተባባሪ አካላት በኮሚሽኑ ተግባር እና ኃላፊነት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው ብለዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎችም በሶማሌ ክልል11 ዞኖች፣ 96 ወረዳዎችና 6 የከተማ አስተዳደሮች በሚካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ ላይ ይሳተፋሉ ነው ያሉት።

ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉ ተባባሪ አካላት ወደየወረዳዎቹ ሲመለሱ ግልፅ፣ ፍትሀዊ፤ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ እያንዳንዱ ተባባሪ አካል 10 ተሳታፊዎችን እንደሚለይ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ በክልሉ በቀጣይ ለሚካሄዱ ተግባራት ስኬታማነት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

የተባባሪ አካላት ስልጠናው ከኅዳር 4 እስከ ኅዳር 6 የሚቆይ ሲሆን፤ በሀገራዊ ምክክር አስፈላጊነት፣ በተባባሪ አካላት ኃላፊነት እና በሀገራዊ ምክክር ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ላይ ያተኮረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከኅዳር 11 እስከ 13 ተመሳሳይ ስልጠና በክልሉ ጎዴ ከተማ እንደሚካሄድ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ስልጠናው ከዚህ ቀደም የአቅም ግንባታ ስልጠና በወሰዱ የቀብሪደሀር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ይሰጣል።

በስልጠናው ከክልሉ ምሁራን መድረክ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 824 ሰዎች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ኮሚሽኑ እስካሁን በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች ከ5 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች መምረጡንም አምባሳደር መሀሙድ ድሪር አስታውሰዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top