በሀገራዊ ምክክሩ በ1 ሺህ 400 ወረዳዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉ እየተሰራ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

11 Mons Ago 573
በሀገራዊ ምክክሩ በ1 ሺህ 400 ወረዳዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉ እየተሰራ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

በኢትዮጵያ በ1 ሺህ 400 ወረዳዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የ4 ወራት የስራ አፈጻጸም ሂደት፣ የተገኙ ስኬቶችና የገጠሙ ችግሮች ላይ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ በዝግጅት ምዕራፍ የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በተለያዩ ክልሎች በመካሄድ ላይ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ በምክክሩ የሚሳተፉ አካላት ልየታን ከቀበሌና ከጎጥ ጀምሮ አካታችና ተዓማኒ በሆነ መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ለዚህ ስኬት የሃይማኖት አባቶች፣ እድሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመምህራን ማህበራት እና የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ዘጠኝ የማህበረሰብ ክፍሎች ተለይተው እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ የልየታ ሂደት በተለያየ ምክንያት ከቀድሞ መኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችንም የማካተት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን አክለውም፥ በሀገራዊ ምክክሩ በሀገሪቱ 1 ሺህ 400 ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተወካዮቻቸው አማካይነት በተገቢው ሁኔታ እንዲሳተፉ ይደረጋል ነው ያሉት።

የሀገራዊ ምክክር ዓላማና ሂደትን በተመለከተ በተለያዩ ቋንቋዎች ለህብረተሰቡ የማስገንዘብ ተግባርም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top