ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እቅድ መሳካት የመገናኛ ብዙኃን ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

12 Mons Ago 434
ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እቅድ መሳካት የመገናኛ ብዙኃን ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

ለአገራዊ ምክክሩ እቅድ መሳካት የመገናኛ ብዙኃን ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠየቀ።

"የሚዲያ ሚና ለአገራዊ ምክክርና ብሔራዊ መግባባት" በሚል መሪ ኃሳብ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ አየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች፣ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ከዝግጅት እስከ ተሳታፊ ልየታ የተሳካ ሥራ አከናውኗል ብለዋል።

ከዝግጅት ምዕራፍ በመነሳት በርካታ ሥራዎችን በማሳካት ሁለተኛውን ምዕራፍ ደግሞ በማገባደድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለምክክር ሂደቱ ስኬት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በእስካሁኑ ሂደት ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመሥራት የተሳካ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የኮሚሽኑን ሥራዎች ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ የሚዲያዎች ሚና የላቀ በመሆኑ፤ እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች ላይ አዎንታዊ ሚና ለተጫወቱ መገናኛ ብዙኃን ምስጋና በማቅረብ በቀጣይ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ለምክክር ሂደቱ መሳካት የሰላም ጉዳይ መሰረታዊ በመሆኑ አጠቃላይ ሕዝቡ የሰላም ዘብ እንዲሆን ጠይቀው፤ በተለይም ሚዲያዎች በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top