የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ህዝቦች በሀገራቸው ጉዳይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

1 ዓመት በፊት 291
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ህዝቦች በሀገራቸው ጉዳይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከልሂቃንና ፖለቲከኞች በተጨማሪ ህዝቦች በሀገራቸው ጉዳይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የምክክር ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋና ምስራቅ ቦረና ዞኖች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየመከረ ይገኛል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደገለፁት ኮሚሽኑ ከልሂቃንና ፖለቲከኞች በተጨማሪ ህዝቦች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ ነው።

የዛሬው መድረክም ባለድርሻ አካላት በተሳታፊዎች ልየታና በአጀንዳ ማሰባሰብ ዙሪያ ግልጽ ግንዛቤ እንዲይዙና በምክክሩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ነው ብለዋል።

በመድረኩ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ የሲቪክና ህዝባዊ ተቋማት፣ የፖለቲካ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ሁሉም ተሳታፊዎች በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎች ላይ ግብዓት እንዲሰጡ የተዘጋጀ እንደሆነም ገልጸዋል።

''ሁሉም ስለ ሀገሩ ሀሳብ መስጠት አለበት'' ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ሁሉንም የሕብረተስብ ክፍል በማሳተፍ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሀሳብ በማውጣት በምክክር ወደ አንድ ለማምጣት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የምክክር ሂደቱ ከአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቱ ጀምሮ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ኮሚሽኑ በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top