በፓኪስታን ኢስላማባድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ መመረቁን የኢ.ፌ.ደ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በተለያዩ የትብብር መስኮች ግንኙነታቸውን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጠናከሩ የመጡት ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን አዳዲስ የግንኙነት ምዕራፎችን እየከፈቱ ይገኛሉ።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ካራቺ የጀመረ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በኢስላማባድ ከአንድ ዓመት በፊት የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዛሬ በይፋ ተመርቋል።
ኤምባሲውን መርቀው የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሂና ራቢኒ ካሃን ናቸው።
በኢስላማባድ ተቀማጭ የሆኑ የዳኘሎማሲ ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት የምረቃ ስነስርዓት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የኤምባሲው በይፋ መመረቅ በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ግንኙነት አዳሲ ዲኘሎማሲ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ከሁለትዮሽ ባሻገር በጋራ የሚሰሩባቸው በርካታ ዓለምአቀፍ የጋራ ጉዳዮች እንዳሉ ያስታወሱት አምባሳደር ምስጋኑ፤ የኤምባሲውም መከፈት ግንኙነቱን ለማስፋት እና ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።
የተጀመሩ የንግድ፣ የኢንቬስትመንት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎችን እንዲጠናከሩ ኤምባሲው እንደሚሰራ የጠቆሙ ሲሆን፣ ግንኙነቱን አሁን ካለበት ይበልጥ ለማጎልበት የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሂና ራቢኒ ካሃን ደግሞ፣ ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ተመሳሳይ የልማት እና ኢኮኖሚ ፈተና ያለባቸው ሃገሮች መሆናቸውን በመጠቆም ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄን ለመፈለግ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ የኢትዮጵያ የኤምባሲ በኢዝላማባድ መኖር ከሁለቱ ሃገራት ባሻገር ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ሚኒስትር ዲኤታዋ ተናግረዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ደግሞ፣ ኤምባሲው ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በይፋ ለምረቃ እንዲበቃ የፓኪስታን መንግስት ላዳረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ኤምባሲው ለዘላቂ የሁለቱ ሃገራት ጥቅም መሰረት መሆኑንም አምባሳደር ጀማል አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ በ1950ዎቹ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።