ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ የፓሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች ነው

11 Mons Ago
ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን  የበለጠ ለመሳብ  የፓሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች ነው

ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ የፓሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የቢዝነስ ፎረም ዛሬ በፓኪስታን ካራቺ መካሄድ ጀምሯል።

ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት ይበልጥ በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይ አትኩሮ በመካሄድ ላይ ነው።

በፎረሙ መክፈቻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲኘሎማሲያዊ እና የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ባለፉት አምስት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ የፓሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኑንም ገልጸው፣ ዕድሉን የፓኪስታን ባለሃብቶች እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

በፓኪስታን እና በኢትዮጵያ መካከል የተሳለጠ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም አምባሳደሩ አንስተዋል።

የፓኪስታን ንግድ እና ልማት ባለስልጣን ሚኒስትር ዲኤታ ዙቤር ሞቲዋታ በበኩላቸው፣ ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ባላት ግንኙነት ኢትዮጵያ ቁልፍ ሀገር መሆኗን ጠቁመው ሀገራቱ ያላቸውን እምቅ እና ተነፃፃሪ የቢዝነስ አቅም በመጠቀም የንግድ ልውውጣቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።

በፎረሙ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት እና የቢዝነስ አማራጮች እና ምቹ ሁኔታዎች ገለፃ እና ውይይት መደረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በፎረሙ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top