ጾም እና የጾም ወቅት አመጋገብ

1 Mon Ago
ጾም እና የጾም ወቅት አመጋገብ

ባሳለፍነው ሳምንት በክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የዐቢይ ጾም እና የረመዳን ጾም ተጀምሯል፤ የሁለቱም ጾም በአንድ ቀን መጀመሩን ተከትሎ አጋጣሚው ብዙዎችን ሲያስደንቅም ነበር፡፡

ጾሙን የሚጾሙ ሰዎች የሚጾሙበት ምክንያት መንፈሳዊ እና ሰማያዊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ በጾም ወቅት የሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች የየራሳቸው የአመጋገብ ሥርዓት አላቸው፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ በጾም ወቅት ሰዎች አመጋገባቸውን በተመለከተ ምን መምሰል አለበት የሚለውን እንመለከታለን፡፡ ፆም ለጤና ጥቅም እንዳለው የሥነ-ምግብ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

በፆም ወቅት መብላት ያለብንን እና የሌለብንን እንዲሁም፣ መቼ መብላት አለብን በሚሉት ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚደረግ ቢሆንም፣ ዋና ሀሳቡ በየቀኑ ለተወሰኑ ሰዓታት ያክል ምግብ የሚባል አለመቅመስ የሚለው ነው።

ጾም ከሃይማኖታዊ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ለተወሰኑ ሰዓታት ከምግብ ርቆ መቆየት ጠቀሜታ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎችም ይናገራሉ፡፡

ሰውነታችን ያከማቸውን ስኳር ከተጠቀመ በኋላ የቀረው ወደ ስብ ይለወጣል፤ ይህ ስብ ካልተቃጠለም አላስፈላጊ የሰውነት ክብደት እና በሽታ ይከሰታል፡፡

በጾም ወቅት ከምግብ ርቀን ስንቆይ ይህ አላስፈላጊ ስብ ይቃጠላል፡፡ ስብ ሲቃጠል ደግሞ አላስፈላጊ ክብደት መቀነስ እና እንደ ስኳር ያሉ በሽታዎችን ለመከላከል ይረዳል። ይህ ሂደት ሜታቦሊክ ስዊቺንግ ይባላል።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በፆም ወቅት ከምግብ ርቀን ስንቆይ ከሚገኙት የጤና ጥቅሞች መካከል የደም ግፊት መቀነስ እና የኮሌስትሮል መጠን መረጋጋት ዋናዎቹ ናቸው።

በሌላ በኩል በሂደቱ አመጋገብን ማስተካከል ሰውነታችን በጾሙ እንዳይዳከም ለማድረግ እንደሚያግዝ ይነገራል፡፡

ከጾም በኋላ የሚቀርቡ የምግብ ዓይነቶች በጾም የተዳከመውን ሰውነት ማበርታት የሚችሉ መሆን እንዳለባቸውም ይመከራል፡፡

እንደ ውሃ እና የተፈጥሮ የፍራፍሬ ጭማቂ ያሉ መጠጦች ማዘውተር ከጾም በኋላ ሰውነታችን አስፈላጊውን እርጥበት እንዲያገኝ ያግዛል፡፡

 

በረመዳን ጾም ወቅት እንደሚደረገው ቴምር መብላት ለሰውነት የኃይል ብክነት ማካካሻ ለማግኘት ይረዳል፡፡

ፕሮቲን ያላቸውን ምግቦች በጾም ወቅት መጠቀሙም ይመከራል፡፡ የተቀቀለ ዶሮን ከተጠበሰ አትክልት ጋር ወይም የተጠበሰ አሳ፣ ቡናማ ሩዝ እና የተጠበሱ አትክልቶች በረመዳን ወቅት ከሚመከሩ ምግቦች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተመሳሳይም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚበሉ ኃይል እና ጥንካሬ የሚሰጡ ምግቦች አሉ፡፡

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ የጾም ወራት ሥጋን፣ ወተትን እና የወተት ተዋጽኦን ሳይጨምር ጥሩ ጣዕም ያላቸው ለጤና በጣም ተስማሚ የሆኑ የምግብ ዓይነቶች መመገብ የተለመደ ነው።

ከነዚህ ምግቦች መካከልም የምስር እና የሽሮ ወጥ፣ የተልባ እና የሱፍ ፍትፍት፣ የሽንብራ አሳ፣ ህልበት እና ስልጆ፣ አዚፋ እና ቃርያ ስንግ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የአመጋገብ ሥርዓቶች እንደ እምነትና ባህል ይለያዩ እንጂ ጥቅሞቻቸ ተመሳሳይ እንደሆነ የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ሰውነታችን ለረጅም ሰዓታት ከቆየ በኋላ ቶሎ ቅባታማ ምግቦችን መመገብ አይበረታታም፡፡

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top