የመርካቶው ነፃ አውጭ - ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ

9 Mons Ago 1348
የመርካቶው ነፃ አውጭ - ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ

ኢትዮጵያ በየዘመኑ ስሟን ከፍ የሚያደርጉ ጀግኖች አጥታ አታውቅም፡፡ ጀግንነት በየፈርጁ ነው፡፡ እንዳንዱ በጦር ሜዳ ውሎ የሀገሩን ጠላት በማንበርከክ የሀገርን ክብር ያስጠብቃል፤ ሌላው ወገኑን ከችግር በማዳን ለወገን ደራሽነቱን ያስመሰክራል፤ አንዳንዱ ደግሞ በዓለም አደባባይ የሀገሩን ሰንደቅ ዓለማ ከፍ የሚያደርግ ተግባር ፈፅሞ የሀገሩ ኩራት የወገኑ መመኪያ ይሆናል፡፡

ሌላው ደግሞ ሀገሩ የምታድግበትን ሀሳብ አመንጭቶ ወደ ተግባር በመለወጥ የብዙ ወገኖቹን ሕይወት እና የሀገሩን ሁኔታ የሚለውጥ ተግባር ይፈፅማል፡፡ ከእነዚህ ጀግኖች መካከል ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ አንዱ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የችርቻሮ ንግድ የጀመሩት በአብዛኛው ከየመን የመጡ ዓረቦች እንደሆኑ ታሪክ ዋቢ ነው፡፡ እነዚህ ዓረብ ነጋዴዎች ግን ቀስ በቀስ ሁሉንም ነገር እየተቆጣጠሩ መሄዳቸው ሁኔታውን አሳሳቢ አደረገው፡፡ ይህ ሂደት እንዲቀየር እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅትም ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ የተባሉ ለሀገራቸው አሳቢ ልበ ቀና ሰው ተገኙ፡፡

ፊታውራሪ ሩጋ ‘የንግድ ሥራውን ከዓረቦች እጅ እንዴት ወደ ኢትዮጵያውያን እንመልስ?’ በሚል በተነሳ ሀሳብ ላይ ሥራውን በተገቢው ሁኔታ በመተግበር ከየመኖች ሊረከቡ የሚችሉት ኢትዮጵያውያንን ወደ ዘርፉ ያመጡ ባለራዕይ ነበሩ፡፡

ልጃቸው ከፒቴን መስፍን ሩጋ በሰጡን መረጃ መሰረት ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ የተወለዱት መስከረም 5 ቀን 1911 በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በሐይቆች እና ቡታጅራ አውራጃ በሶዶ ወረዳ ጢያ ቀበሌ ነው፡፡ አባታቸው ቀደም ብለው በማረፋቸው በ6 ዓመታቸው ከእናታቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለሶስት ዓመታት ፊደል ከቆጠሩ በኋላ አሊያንስ ፍራንሴዝ ትምህርት ቤት በመግባት ለአምስት ዓመት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በመቀጠልም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቀበና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር የኪስ ገንዘብ እየተቆረጠላቸው ለስድስት ወራት እንደተማሩ ለሬድዮ ቴሌግራፊስትነት ምልመላ ሲደረግ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተመርጠው ቀድሞ አቡጀዲ ፋብሪካ በኋላ አርማ ጋራዥ የተባለ ቦታ በአንድ እንግሊዛዊ ካፕቴን የበላይ ኃላፊነት በሚመራ ትምህርት ቤት በመግባት የሬድዮ ቴሌግራፊስት ትምህርት በመከታተል ላይ እንዳሉ ሀገራችን በፋሺስት ጣልያን በመወረሯ ትምህርት ቤቱ ሲዘጋ ትምህርታቸውን አቋረጡ።

ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ተሸንፋ ኢትዮጵያን የለቀቀችበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ‘የዓረብ ቤት’ እያሉ የሚጠሯቸው የዓረብ ሸቀጣሸቀጥ መደብሮች እጅግ እየተስፋፉ የሄዱበት ወቅት ነበር። እንደዚህ ዓይነቱ ንግድ በውጭ ዜጎች ሲያዝ ኢትዮጵያውያንን የሚጎዳቸው መሆኑን የተገነዘቡት አቶ መኮንን ሀብተወልድ እሳቸው በሚመሩት ንግድ ሚኒስቴር ውስጥ ሰፊ ጥናት ተደርጎ አንድ መፍትሔ እንዲገኝለት ልዩ ኮሚቴ አቋቋሙ።

የአቶ መኮንን ሀብተወልድን ያሳሰባቸው የንግዱ በዓረቦች መያዝ እና የነሱ በኢትዮጵያውያኑ መብት መክበር ብቻ ሳይሆን፣ ዓረቦቹ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ያሉ ሴት ልጆችን በገንዘብ እየደለሉ እንደ ሚስት በመያዝ ብዙ ልጆችን ከወለዱ በኋላ ለተወለዱት ልጆች እና እናቶቻቸው ምንም መተዳደሪያ ሳይሰጡ ያከማቹትን ገንዘብ ወደ ሀገራቸው በማስተላለፍ ንግዱን ደግሞ ለሌላ ዓረብ ወገናቸው በመስጠት ከሀገር መውጣታቸው የፈጠረው ማኅበራዊ ቀውስም ጭምር ነበር።

የንግድ ሚኒስቴር ኃላፊዎች እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገር ፍቅር ማህበር አባሎች የተገኙበት ኮሚቴ ባካሄደው ጥናት ዓረቦቹ የንግድ ሥራቸውን የጀመሩት ከጣሊያን ወረራ በፊት ቢሆንም፣ ጣሊያን ደግሞ በአምስቱ ዓመት ቆይታው ንግዳቸውን እንዲያስፋፉ በገፍ የንግድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው በማድረጉ ሁሉንም የንግድ ዘርፍ መቆጣጠራቸውን በጥናቱ አመለከተ፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከእንግዲህ ለውጭ ሀገር ተወላጆች አዲስ የችርቻሮ የንግድ ፈቃድ እንዳይሰጥ አዲስ አዋጅ በማውጣት፣ ፈቃድ ያላቸውም የያዙት ፈቃድ ጊዜው እስከሚያልቅ ድረስ ብቻ ሥራቸውን መቀጠል እንደሚችሉ ማስታወቅ የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን ኮሚቴው የውሳኔ ሀሳብ አቀረበ።

የንግድ ሚኒስትሩ ለውጭ ሀገር ዜጎች የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ መከልከሉን አዋጅ ማውጣት አስፈላጊነት ቢያምኑበትም፣ ንግዱን ሙሉ በሙሉ የሚረከቡ ኢትዮጵያውያን እስካልተተኩ የችግሩ የመጨረሻው መፍትሔ አለመሆኑን በማመን ኢትዮጵያውያን ሥራው የሚረከቡበትን ዘዴ እንዲፈለግ ኮሚቴው ጥናቱን እንዲቀጥል አዘዙ። ኮሚቴው ቃለ ጉባኤ ያዥ ሆነው እንዲሠሩ አቶ መኮንን ሀብተወልድ የመረጧቸው ሩጋ አሻሜ የተባሉ ወጣት ዓረቦቹ የያዙትን የችርቻሮ ንግድ ማስለቀቅ የሚችሉት የትውልድ አካባቢው ተወላጅ ጉራጌዎች ናቸው የሚል የመፍትሔ ሀሳብ አመጡ።

ሀሳባቸውንም የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የእርሻ ሚኒስትር ለሆኑት አቶ መኮንን ሀብተወልድ ብርቱ ሚስጥር በሚል ማስታወሻ እንደሚከተለው ገለጹ። “ጌታዬ የተጨነቁበትን ጉዳይ እኔም በአቅሜ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ያለማቋረጥ ሳስብበት ቆይቻለሁ። ለችግሩ መድሀኒት ተፈልጎ በአስቸኳይ እንዲቀርብልዎ ጌታዬ መመሪያዎን እና አደራዎን ለኮሚቴው ሲሰጡ ኃላፊነቱ የሁላችንም ነው። በእኔ በትንሹ ሠራተኛዎ አስተያየት በገዛ ሀገራችን በችርቻሮ ንግድ የወረሩንን እነዚህን ዓረቦች ማስለቀቅ እና ማሰናበት የምንችለው ከኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ለጊዜው ቁጥራቸው አምሳ የሚሆኑትን ወጣት ጉራጌዎች መርጠን ዓረቦቹ በከፈቷቸው ሱቆች አጠገብ ተመሳሳይ ሱቅ እየከፈቱ ነዋሪውን ህዝብ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ እና በዋጋ ቅናሽ እየማረኩ በርትተው ሲሰሩ ነው። ዓረቦቹ በዚህ አኳኋን የመጣባቸውን ውድድር ተቋቁመው ለማሸነፍ ስለማይችሉ ሱቆቻቸውን እየዘጉ በሰላም ወደሀገራቸው ከመመለስ በስተቀር ሌላ ምርጫ አይኖራቸውም። ትግላችንን በዚህ ሁኔታ እንድንቀጥል ክቡርነትዎ የሚስማሙበት ከሆነ ለሥራ የሚመረጡት ጉራጌዎች በየተወለዱበት አካባቢ በሚገኙት ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች የታመኑ እና ዋስትና የሚሰጣቸው ስለሚሆኑ ለንግዳቸው ማቋቋሚያ ወጭው ተተምኖ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ብድር መንግስት ሊሰጣቸው የሚገባ ይሆናል።

እኔን ትንሹን ሠራተኛዎን የኮሚቴው ቃለ ጉባዔ ያዥ እና ፀሐፊዎ አድርገው ለሰጡኝ ሹመት ይህንን ሐሳቤን ለአባሎቼ አቅርቤ መከራከር ባልቸገረኝ ነበር። ነገር ግን ጌታዬ እንደሚያውቁት የዓረቦቹን ንግድ ተወዳድረው የሚያሸንፉት ጉራጌዎች ስለሆኑ ኃላፊነቱ ለእነሱ ቢሰጥ ይሻላል ብዬ ስናገር ‘ሩጋ አሻሜ ተሻምቶ ለተወላጆቹ አደላ’ ብለው እንዳያፌዙብኝ በማሰብ ነው።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተግባሩ ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ አንድነት መጣር የመጀመሪያ ግዳጁ መሆኑን አውቃለሁ። በዚህም መሰረት ሀገራችን የምትለማው እና የምታድገውም በየአውራጃው ያለው ኢትዮጵያዊ በሞያው እና በዝንባሌው ተግቶ ሲሠራ ነው ብዬ አምናለሁ።

እኔም ከዓረብ ነጋዴዎች ጋር ለሚያስፈልገው ውድድር ተወላጆቼ ጉራጌዎች የተሻሉ ይሆናሉ ብዬ ስናገር ሞያቸውን እና ችሎታቸውን በመመርኮዝ እንጂ በተለይ ወገኖቼን ለመጥቀም በተመሠረተ ሐሳብ ላይ አለመሆኑን ጌታዬ እንደሚገነዘቡልኝ ዕምነቴ ሙሉ ነው።” በማለት ሀሳቡን በጽሑፍ አቀረቡ፡፡

አቶ መኮነን ሀብተወልድ ወጣቱ ሩጋ ባቀረቡላቸው ሐሳብ በጣም ተማረኩ። በማግስቱም በጽ/ቤታቸው ኮሚቴውን ሰብስበው የሩጋ አሻሜን ስም ሳያነሱ ከአንድ ትጉህ ሠራተኛዬ የቀረበልኝ በሚል መነሻ ሐሳቡን ተንትነው ለአባሎቹ ገለፁ። በመጨረሻም “እኔ በቀረበልኝ ሐሳብ ተስማምቼበታለሁ። እናንተ የአፈፃፀሙን ቅደም ተከተል በዝርዝር አጥንታችሁ በአንድ ሳምንት ውስጥ እንድታቀርቡልኝ” የሚል ውሳኔ ሰጥተው ስብሰባውን አበቁ።

በወጣቱ ሩጋ አሻሜ እና በጓደኞቻቸው ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርጠው የቀረቡት አርባዎቹ የጉራጌ ነጋዴዎች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ተቀብለው በአዲስ አበባ ከተማ ሥራቸውን በአስቸኳይ እንዲጀምሩ እና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚሰጡት ውጤት ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት የኮሚቴው አባሎች በሙሉ ከስምምነት ላይ ደረሱ።

እነዚህም አርባዎቹ ወጣት ነጋዴዎች በየሠፈሩ ከሚገኘው ‘ዓረብ ቤት’ አጠገብ፤ ሱቅ እንዲያቋቁሙ ንግዳቸውን ለመጀመር ወደፊት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሚያገኙት ትርፍ የሚከፍሉት ለእያንዳንዳቸው ሰባት መቶ የኢትዮጵያ ብር መንግሥት እንዲያበድራቸው ኮሚቴው የተስማማበትን መኮንን ሀብተወልድ ለንጉሠ ነገሥቱ አቅርበው አስፈቀዱ።

እንደታሰበው ጉራጌዎቹ ነጋዴዎች በየዓረቡ መደብር አጠገብ ሱቆቻቸውን እየከፈቱ ንግዳቸውን ሲጀምሩ ህዝቡም ደንበኝነቱን ከነሱ ጋር ስላጠናከረ በትጋት እና በጋለ ስሜት መሥራት ጀመሩ። አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ከአርባዎቹ ጉራጌዎች መካከል ሰላሳ ሦስቱ በዓረቦቹ ተይዞ የነበረውን ንግድ በሙሉ ስለተቆጣጠሩ ዓረቦቹ የነበራቸውን ሱቅ እየዘጉ ከየሠፈሩ መውጣት ግዴታ ሆነባቸው።

ኢትዮጵያውያኖቹ ነጋዴዎች ሕዝቡ ለዕለት ኑሮው የሚያስፈልጉትን ሁሉ ከየዓረብ ቤት በተሻለ አኳኋን አሟልተው መገኘታቸው ብቻ ሳይሆን፣ መጠነኛ የሆነ የዋጋ ቅናሽ በማድረጋቸውም ተጠቃሚዎቹን ለመማረክ ችለዋል።

ንጉሠ ነገሥቱ ለተመረጡት አርባ ነጋዴዎች የፈቀዱት 28 ሺህ ብር በብድር ሳይሆን በስጦታ እንዲሰጣቸው ነበር። ነገር ግን በነፃ የተሰጣቸው እርዳታ መሆኑን ነጋዴዎቹ ካወቁ ምናልባት የኃላፊነት ስሜት ላያድርባቸው እና ገንዘቡንም ተቆጣጣሪ የለብንም በማለት ለታሰበው ጉዳይ በትክክል ላያውሉት ይችላሉ የሚል ስጋት ስተፈጠረ ነበር በብድር መልክ በነጭ ወረቀት ፈርመው እንዲወስዱ የተደረገው።

ከአርባዎቹ ነጋዴዎች ውስጥ ሠላሳ ሦስቱ ትርፍ ሲያገኙ ገንዘቡን ለመመለስ ሲቀርቡ የገንዘብ ሚኒስቴር የገቢ ደረሰኝ ካርኒ ካልተቆረጠልን ማለታቸው ለአፈጻፀሙ አስቸጋሪ በመሆኑ ሌላ ዘዴ መፈለግ ግዴታ ሆነ። ዘዴው ተፈልጎ ከመገኘቱ በፊት ነጋዴዎች ቀድመው ለንግድ ሚኒስትሩ አንድ የተለየ ሐሳብ አቀረቡ።

ሀሳቡም፣ “እኛ የሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ነጋዴዎች ለጀመርነው የንግድ ሥራ ማስፋፊያ እንዲሆን አንድ ማኅበር አቋቁመናል። የማኅበራችን ዋና ተግባር መንግስታችን ለእኛ በቀየሰልን መንገድ እና በሰጠን ከፍተኛ ድጋፍ እስካሁን ከፍተኛ ውጤት ስለአገኘንበት ይህንኑ ዓላማ ዜጎች ከሆኑት ነጋዴዎች ጋር ለመወዳደር እንድንችል አስፈላጊውን እርዳታ መስጠት ነው። ስለዚህ መንግሥት ገንዘቡን የሚቀበልበት አሠራር እስሚያዘጋጅ ያቋቋምነው የንግድ ማስፋፊያው ማኅበራችን ይህንን እጃችን ላይ የሚገኘውን ገንዘብ በብድር ተቀብሎ እንዲሠራበት እና ትርፍ ሲያገኝ ለመንግስታችን ገቢ እንዲያደርግ እንዲፈቀድለት ክቡርነትዎን እንለምናለን” በማለት ጠየቁ።

መኮንን ሀብተወልድ ይህን ሐሳብ የተመለከቱት በከፍተኛ አድናቆት ነበር። በአቀራረቡም ስለተደሰቱ፤ ጉዳዩን ለማስፈፀም ጊዜ አልወሰዱም። ልዩ ጸሐፊያቸውን ጠርተው፣ “ይህ የቀረበልኝ ሐሳብ የጉራጌዎችን ንቃት እና ብልህነት ደህና አድርጎ የሚያመለክት ነው። የመስሪያ ቤታችንን የአሠራር ድክመት ተገንዝበው “እምቢ” የማይባል ጥያቄ አቅርበውልናል። በመሰረቱ እኛ የምንፈልገው እነሱ ብርታታቸውን ቀጥለው ዓረቦቹን እንዲያባርሩልን ነው። እስካሁን ያስገኙት ውጤት በጣም ጥሩ ስለሆነ፤ አሁን የጠየቁትን በአቃቤ ሰዓት ለጃንሆይ አቅርቤ እንዳስፈቅድላቸው ማስታወሻው ይዘጋጅልኝ” ብለው ወሰኑ።

አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የንጉሠ ነገሥቱን መልካም ፈቃድ አግኝተው የጉራጌዎቹ ማኅበር ገንዘቡን ተቀብሎ “የዓረብ ቤት” በሚል መጠሪያ በየከተማው የተጥለቀለቀውን ንግድ ቤት በውድድር እያዘጋ የኢትዮጵያውያኑን መብት እንዲያስከብር ሙሉ ዕምነታቸውን ጣሉበት።

በዚህ አኳኋን ጉራጌዎቹ ተጠናክረው ባሳዩት ብርቱ ጥረት የየመን ዓረቦች አብዛኛዎቹ ሱቆቻቸውን እየዘጉ ወደየሀገራቸው ሲመለሱ ጥቂቶች ደግሞ ሌላ ባላንጣ ደርሶ እስከሚያባርራቸው ወደ ዋናው ገበያ ወደ መርካቶ እየተዛወሩ በልዩ ልዩ የጨርቃ ጨርቅ ንግድ ለመቋቋም ሞክረው ነበር። ሙከራቸው ብዙ ሊያቆያቸው ስላልቻለ እነሱም ቀስበቀስ እየለቀቁ ሄዱ።

የጉራጌዎች ንግድ ሥራ አባት በሆኑት ፊትአውራሪ ሩጋ አሻሜ ሀሳብ አፍላቂነት መርካቶን እና ሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢዎችን ነጻ ያወጡት ጉራጌዎች፣ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰኑ በኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞች ሁሉ የንግድ ሥራ ማስፋፋት መገለጫቸው ሆኖ ቀጠለ፡፡ ፊታውራሪ ሩጋ በዚህ ተግባራቸው በኢትዮጵያ የንግድ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በጉልህ ሲነሳ ይኖራል፡፡

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በተደረገ የለውጡ ድጋፍ ሰልፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ስለዚህ ቅን ኢትዮጵያዊ አውስተዋል፡፡ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ ኢትዮጵያ ነጻ ብትወጣም አንድ ብልህ ኢትዮጰያዊ "ገና ያላለቀ ነገር አለ" ብሎ ተናገረ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ከወራሪው ነጻ ብትወጣም መርካቶ አሁንም ነጻ አልወጣም ብሎ ስለ ኢኮኖሚ ነጻነት ፊታውራሪ ሩጋ ያደረጉትን ተጋድሎ አድንቀዋል። 

ብሔራዊ ዐርበኝነት እና ውጤቱ በሁሉም የትግል መስክ የሚከፈል መስዋዕትነት መሆኑን ባነሱበት ንግግራቸው መላው ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው አንድነት፣ እድገት እና ብልፅግና የእነፊታውራሪ ሩጋ አሻሜን መርህ ስለ ኢትዮጵያ ጥቅም እንዲከተሉ አሳስበዋል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top