በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሚታዩ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የተጀመሩ የሪፎርም ትግበራና የዝግጅት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ዛሬ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አመራር ዐቢይ ኮሚቴ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂደናል ብለዋል።
በውይይቱም በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና በመጀመሪያ ዙር የተመረጡ ተቋማት ያከናወኗቸውን የሪፎርም ሥራዎች መገምገማቸውን ገልጸዋል።
የሪፎርም አስተዳደራዊ ሥራዎች፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓትን መዘርጋት፣ የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት አገልግሎቶችንና ውሳኔዎችን ማቀላጠፍ ላይ ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውንም ተመልክተናል ሲሉም ጠቅሰዋል።
በሪፎርሙ የታቀፉ ተቋማትም ያላቸውን ልምዶች የሚቀያየሩበት እና ተቀራርበው የሚሰሩበትን አውድ መፍጠር መቻሉን አንስተዋል፡፡
ተቋማት ያከናወኗቸውን ተግባራት በዝርዝር በመቃኘት ጥንካሬዎችንን ውስንነቶችን ለይተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ላይም አቅጣጫ መቀመጡን ገልፀዋል።