በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በንግግር በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር በተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ በተለይም የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት ስብራቶችን ለማከም ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር የጋራ መግባባት ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተሳካ መልኩ ስራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በንግግር በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስትና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ብልጽግና ፓርቲ በምክክር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ይቻላል የሚል ፅኑ አቋም በመያዝ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመለት ዓላማ ከዳር እንዲደርስ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና እገዛ አስፈላጊ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ከችግርና ጉስቁልና ወጥታ የበለጸገችና ለዜጎቿ የምትመች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት መደገፍና ማገዝ ተገቢ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ በአካታችና አሳታፊነት በኃሳብ የበላይነት እንዲመራ በማድረግ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።