ለ82 ቀናት የዓለማችንን ረጅሙን ምርጫ የምታካሂደው ሀገር- ሕንድ

9 Days Ago
ለ82 ቀናት የዓለማችንን ረጅሙን ምርጫ የምታካሂደው ሀገር- ሕንድ

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ከዓለማችን ግማሽ ያክሉን የህዝብ ብዛት የያዙ 10 ሀገራት ምርጫ ያካሂዳሉ።

ባንግላዴሽ፣ ብራዚል፣ ህንድ፣ አሜሪካ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፓኪስታን፣ ሩሲያ፣ እና ሜክሲኮ ዴሞክራሲያቸውን በምርጫ ያሳያሉ። አንዳንዶቹ ምርጫቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ሂደቱን ጀምረውታል። በእነዚህ ምርጫዎች ከ2 ቢልዮን በላይ የሚሆኑ መራጮች ድምጽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

ሕንድ ረጅሙን እና ዴሞክራሲያዊ የተባለውን ምርጫ እያካሄደች ትገኛለች። ሀገሪቱ በአውሮፓውያኑ 1947 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻነቷን ካገኘች በኋላ የመጀመሪያውን ምርጫ ያካሄደችው ከ1951 እስከ 1952 ሲሆን፣ የዘንድሮ ምርጫ ለአሥራ ስምንተኛ ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል። በ1.4 ቢሊዮን ሕዝብ የዓለምን አንደኝነት ከቻይና የተረከበችው ህንድ ከ2 ሺህ 500 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሯትም አስሩ ብቻ ሎክ ሳባ የተባለውን ምክር ቤት 86 በመቶ መቀመጫዎችን ይይዛሉ።

የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ (INC)፣ ጃናታ ዳል (People’s Party)፣ ባራቲያ ጃናታ ፓርቲ (Indian People's Party)፣ የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ (R)፣ ጃናታ ፓርቲ (People's Party) የተባሉ አምስት ፓርቲዎች በምርጫው ዋነኛ ተፎካካሪዎች ሲሆኑ፣ በታሪክ ምርጫውን በማሸነፍ ብዙ ጊዜ በመምራት የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስን (INC) የሚያክል ፓርቲ የለም።

በማተማ ጋንዲ ተመሥርቶ የነጻነት ንቅናቄውን የመራው እና በህዝቡ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበረው ይህ ፓርቲ ዘጠኝ ጊዜ በማሸነፍ ሀገሪቱን መርቷል። ላለፉት ሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ግን አሁን ሀገሪቱን እየመራ ባለው ጃናታ ዳል (Indian People’s Party) ተሸንፏል።የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ ተፎካካሪ የሆነው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ፓርቲ ባራቲያ ጃናታ ፓርቲ (Indian People's Party) አምስት ጊዜ፣ ቀሪዎቹ ሦስት ፓርቲዎች አንዳንድ ጊዜ በማሸነፍ ህንድን መርተዋል።

የሎክ ሳባ (የሕዝብ ቤት) ወይም የታችኛው የሕንድ ፓርላማ አባላት የሚመረጡት ለምርጫ በደረሱት ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ሲሆን፣ መራጮቹ አካባቢያቸውን ወክለው ከሚወዳደሩ እጩዎች መካከል ይወክለናል የሚሉትን እጩ በነጻነት ይመርጣሉ። በሎክ ሳባ ምርጫ አሸናፊ የሚሆኑት ዕጩዎች የፓርላማ አባል በመሆን ለአምስት ዓመት ይቆያሉ።

543 አባላት ያሉት ምክር ቤቱ በኒው ዴልሂ በሚገኘው የሳንሳድ ባቫን ሎክ ሳባ ቻምበር ውስጥ አዳዲስ ህጎች የማውጣት፣ ከህግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የመከራከር፣ ሁሉንም የህንድ ዜጎች የሚነኩ እና በሥራ ላይ ያሉ ህጎችን የማስወገድ ወይም የማሻሻል ሥራዎችን ይሠራል።

ሚያዚያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም የጀመረው 18ኛው የሀገሪቱ የምክር ቤት ምርጫ በሰባት ምዕራፎች ተከፍሎ እስከ ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ለ82 ቀናት ይካሄዳል። ምርጫው የሚካሄደው አራት ግዛቶችን የሚወክሉ የህዝብ ተወካዮችን ለምክር ቤት ለማብቃት ነው። በእነዚህ ግዛቶች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ይኖራሉ። ምርጫውን አሸናፊ የሚሆነው ፓርቲ መንግሥት ለመመስረት 272 ወንበሮች ማግኘት ይጠበቅበታል። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የመራጮችን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ማስታወቅ አይችልም።

14.4 ቢሊዮን ዶላር የሚወጣበት ውድ ምርጫ፣ በ15 ሺህ 256 ጫማ ከፍታ ላይ የሚገኝ የምርጫ ጣቢያ፣ 2 ሺህ 660 የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት፣ እንዲሁም በሀገሪቱ ሁሉም ጫፎች ለሚካሄደው ምርጫ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ ዝሆንን ጨምሮ ሁሉንም የመጓጓዣ መንገዶች የሚጠቀሙ መሆናቸው ምርጫውን ልዩ የሚያደርጉት ሂደቶች ሲል አልጀዚራ ዘግቧል። ባራቲያ ጃናታ (Indian People's Party)ን የሚመሩት ናሬንድራ ሞዲን የሚፎካከሩት ዋነኞቹ ተቀናቃኞች የህንድ ብሔራዊ ኮንግረስ (INC)፣ አም አድሚ ፓርቲ (AAP)፣ ድራቪዳ ሙኔትራ ካዛጋም (DMK)፣ የመላው ሕንድ ትሪናሙል ኮንግረስ (TMC) ፓርቲዎች እንደሚሆኑ ከወዲሁ ግምት ተሰጥቷል። 

የጋንዲ ኔሩ ትውልድ የሆኑት፣ አባታቸው ራጂቭ ጋንዲ፣ አያታቸው ኢንዲራ ጋንዲ እና ቅድመ አያታቸው ኔሩ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የነበሩት፣ ራሳቸውም ለአራት ተከታታይ የምርጫ ወቅቶች የፓርላማ አባል የሆኑት የ53 ዓመቱ ራሁል ጋንዲ የሞዲ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል።  

ፉክክሩ ከባድ ቢሆንም የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ያሳያሉ። የፖለቲካ የኋላ ታሪክ ከሌለው ቤተሰብ ተነስተው በጥረታቸው ብቻ ለትልቅ ደረጃ መድረስ የቻሉት ሞዲ በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ እንደሆኑ ይነገራል። በ2023 የፒው ምርምር ማዕከል ጥናት መሠረት ከአሥሩ ህንዳውያን አዋቂዎች መካከል ስምንቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ አመለካከት አላቸው ይላል። የሞዲ የግል ታሪክ በመራጮች ዘንድ በተለይም አብዛኛው ህዝብ በሚኖርበት ሰሜን ህንድ መራጮች ዘንድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። የተወለዱት ጉጃራት በምትባል የሰሜን ምሥራቅ መንደር ውስጥ ነው። በዚህች መንደር የሚገኘው ማኅበረሰብ በጥብቅ ማኅበራዊ ግንኙነቱ እና በንግድ የሚታወቅ ሲሆን፣ የሞዲ ቤተሰብ ከፍተኛ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ያልነበረም ጭምር ነው። አባታቸው ዳሞዳርድስ ሙልቻንድ ሞዲ ሻይ ቤት የነበራቸው እና ሞዲም በቫድናጋር ባቡር ጣቢያ ሻይ ይሸጡ እንደነበር ሲናገሩ በኩራት ነው። 

ሞዲ በፖለቲካው ዓለም መታወቅ የጀመሩት በ2001 ሲሆን፣ በዚህ ወቅት በትውልድ አካባቢያቸው በተፈጠረ የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰውን አደጋ ለመቆጣጠር በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በብዙኃኑ ህዝብ ልብ ውስጥ ሊገቡ ችለዋል። የወጡበትን ማኅበረሰብ አለመርሳታቸው ደግሞ የበለጠ ተወዳጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

በ2014 በተደረገው ጠቅላላ ምርጫም የእርሳቸው ጥምር ፓርቲ አብላጫውን ወንበር በማግኘቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ። ወደ ሥልጣን እንደመጡ ትኩረት አድርገው የሠሩት አምራች እንዱስትሪዎችን ማስፋፋት እና ኢኮኖሚውን የግሉ ዘርፍ እንዲመራው ማድረግ ነበር። ሌላው የወሰዱት እርምጃ በወቅቱ ሥራ ላይ የነበረውን ገንዘብ መቀየር ሲሆን፣ በዚህም ያላአግባብ በተለያዩ ቡድኖች እጅ ተከማችቶ ለወንጀል መስፋፋት ምክንያት የነበረውን የገንዘብ ምንጭ ማድረቅ ችለዋል። ባደረጓቸው ማሻሻያዎች የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት መነቃቃቱ ይነገራል። በዚህም ከ250 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከከፋ ድህነት እንዳወጡ ይነገርላቸዋል። ወንጀል እና ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰም ሲኤንኤን ባደረገው ጥናት አመላክቷል።

በተለይ ደግሞ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን፣ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እና የባሕር ኃይል ፕሮጀክቶችን በመገንባት እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤቶችን ግንባታ ድጎማ በማድረግ ሀገራቸው ለዜጎቿ ምቹ እንድትሆን አድርገዋል።

በእርሳቸው አመራር ህንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷ በመጨመሩ እንደ ቡድን 20 እና ብሪክስ ባሉ ዓለም አቀፍ ቡድኖች ላይ ያላቸው ተፅዕኖ እየጎላ መጥቷል። ቡድን 20 አካታች እንዲሆንም በግንባር ቀደምትነት እየሠሩ ነው። በዚህም የአፍሪካ ህብረት የቡድን 20 አባል እንዲሆን ትልቁን ኃላፊነት የተወጡት ሞዲ ስለመሆናቸው ተደጋግሞ ተነስቷል።

ህንድ በሕዋ ምርምር ዘርፍም ቢሆን ኃያላኑ ብቻ በነበሩበት በተለይ ጥልቅ የሕዋ ምርምር ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ የህንድ ምርምር እንዲጀመር ማድረጋቸው በጉልህ የሚነሳ አበርክቷቸው ነው። በመከላከያው ዘርፍም የሀገሪቱን የኃይል ሚዛን ማስጠበቅ የቻሉ ሲሆን፣ ከምዕራባውያን ተፅዕኖ ነጻ ሆና እየተንቀሳቀሰች ነው። እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ዘጠነኛ ላይ የነበረችውን የህንድ ኢኮኖሚ ወደ አምስተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያስመነደጓት እኚሁ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ይነሳል።

እናም በእነዚህ መልካም ስራቸው በህንዳውያን የሚመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ለሦስተኛ ዙር ዕድሉን ካገኙ የህንድን ኢኮኖሚ ወደ ሦስተኛ ደረጃ እንደሚያሳድጉ ለመራጮቻቸው ቃል ገብተዋል። አሁን የህንድ አምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት በ17 በመቶ እድገት በእስያ 3ኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ነው። የኢኮኖሚ ግስጋሴዋ በዚህ ከቀጠለ በ2075 የዓለማችን ቁጥር ሁለት የኢኮኖሚ ባለቤት ልትሆን እንደምትችል ትንበያዎች ያመላክታሉ።

በሞዲ ዘመን ታዲያ ስኬቶች እንዳሉ ቢነሱም እየጨመረ የመጣው የወጣቶች ሥራ አጥነት እና በዜጎች መካከል የተፈጠረው የሰፋ የኑሮ ልዩነት ፈተናዎች እየሆኑ ስለመሆኑ ይነሳል። በተለይ ደግሞ በገጠር የከፋ ድህነት ትልቁ ጥያቄ እና የጉዟቸው እንቅፋት ሊሆንባቸው እንደሚችል ተገምቷል። የሞዲ ዘመን በሃይማኖታዊ አድልኦ መተቸቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላኛው ራስምታት እንደሚሆን ይጠበቃል። በሀገሪቱ የሚገኙ 230 ሚሊዮን ሙስሊሞች እንደ አናሳ መቆጠራቸው እና በየጊዜው እያደገ የመጣው ሙስሊም ጠልነት ስደትን ያካተተ ስለመሆኑ ተቺዎቻቸው የሚያነሱት መከራከሪያ ሆኗል። 

በሌላ በኩል ያላቸውን የመንግሥት ሥልጣን በመጠቀም መንግሥታዊ መዋቅሮች ምርጫው ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ እየሠሩ ነው በሚል ይከሰሳሉ። ተፎካካሪዎች ሰፊውን የሀገሪቱ የቆዳ ስፋት አካለው የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ እጅ ሲያጥራቸው የሞዲ ፓርቲ ግን ያለውን የመንግሥት መዋቅር እና ሀብት ተጠቅሞ ተፎካካሪዎቹ ላይ ጫና እያደረገ ይገኛል ተብሎ ይተቻል። የምርጫው ቀናት መራዘም ደግሞ ለእንደዚህ ዓይነቱ የገዢ ፓርቲ ተፅዕኖ እንደሚያጋልጠው የሀገሪቱ ፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት ብዙ ህንዳውያን የሞዲ የዘንድሮ የምርጫ ተሳትፎ በ2012 ከወጣው “Dictator” ከተሰኘ ፊልም ገጸ ባሕሪ ጋር በማነጻጸር ብቻቸውን ተወዳድረው ብቻቸውን እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል ባይ ሆነዋል። በእርግጥ ይህ ፊልም ጸረ ዴሞክራሲያዊ ለሆኑ ሀገራት ጥሩ ማሳያ ቢሆንም በተለይ በፊልሙ ላይ መሪ ገጸባህርይው የኦሎምፒክ ውድድርን ራሱ አዘጋጅቶ፣ ተፎካካሪዎቹን በማስወገድ ብቻውን ሮጦ ሁሉንም ሜዳሊያዎችን የሚወስድ መሆኑ የሞዲ ምርጫ ውድድር ይህን ይመስላል የሚሉ ተንታኞችም ተቃዋሚዎችም አያሌ ናቸው። ሞዲም በአሁኑ ምርጫ ብዙ ተፎካካሪዎቻቸው በተዳከሙበት ሁኔታ ምርጫውን ብቻቸውን ተወዳድረው እንዳሸነፉ ይቆጠራል ይላሉ። የሆነ ሆኖ ይህ እንከን የህንድ ምርጫ ትልቅ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሁሉን አሳታፊ ነው የሚለውን ያስቀረው ይሆን ወይስ የሞዲ የስኬት መንገድ እውቅና ተሰጥቶት ይቀጥላሉ የሚለው በመጨረሻው ውጤት የሚወሰን ይሆናል። 

በለሚ ታደሰ        


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top