6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ /ማሻሻያ/ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ረቂቅ አዋጁን አስመልክተው ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 ለልማት ተነሺዎች ከሚከፈለው የካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የመሰረተ ልማት ገንቢው ተቋም ላይ አላስፈላጊ ጫና እና የጊዜ ብክነት እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የፌዴራል መንግስት ለሚያከናውናቸው የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ማስፋፊያ ስራ ንብረት የመገመት፣ የመክፈል እና የማስነሳት ስራ ሙሉ በሙሉ ለክልል/ለከተማ አስተዳደር አካላት መስጠትና የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርግ አሰራር መዘርጋት በማስፈለጉ ነባሩ አዋጅ ላይ የተወሰኑ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉ ነው አቶ ተስፋዬ ያብራሩት፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የማሻሻያ አዋጁን አስፈላጊነት እና የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ በትኩረት ሊያየው ይገባል ያሏቸውን አስተያየቶች ያቀረቡ ሲሆን ቀደም ሲል የነበረው አሰራር በመንግስት ላይ አላስፈላጊ ወጪዎችን ማስከተሉ እንዲሁም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቁ አለማስቻሉን አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አንዳንድ ክልሎች የካሳ ክፍያ ማከናወን ቀርቶ የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ ለመክፈል እየተቸገሩ በመሆኑ፤ የካሳ ክፍያ ላይ የፌዴራል መንግስት እና ክልሎች በቅንጅት የሚሰሩበት ሁኔታ ቢኖር የተሻለ እንደሆነ ነው የምክር ቤቱ አባላት ያነሱት፡፡
የማሻሻያ አዋጁ በዋናነት ለከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ገዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በተባባሪነት ደግሞ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መመራቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።