በሰሜናዊው የስዊድን ክፍለ ግዛት ውስጥ በምትገኘው የኪሩና ከተማ ሰማይ ላይ ከሰሞኑ የታየው የብርሃን ህብረ ቀለማት የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነው፡፡
ክስተቱ በጠፈር ተመራማሪዎች አገላለፅ "አውሮራ" እየተባለ የሚጠራ ሲሆን፤ ከፀሀይ ወለል ላይ የሚነሱ በአይን የማይታዩ ቅንጣቶች ከምድር የመግነጢሳዊ መስክ ጋር በሚፈጥሩበት ሰበቃ ወይም ፍሪክሽን የሚፈጠር ክስተት ነው፡፡
ተመራማሪዎች እንደሚገልፁት በተለያዩ ግዜያት ከፀሀይ ወለል ላይ የሚነሱ በአይን የማይታዩ "ፕላስማ" የተባሉ ቅንጣቶች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ ቅንጣቶች በሰአት 1,609,344 ኪ.ሜ የመጓዝ ፍጥነት አላቸው።
ቅንጣቶቹ ወደ ምድራችን የሚመጡት በነፋስ መልክ ሲሆን ይህ ነፋስ (Solar wind) ወይንም ሞቃት የፀሀይ ነፋስ ተብሎ ይጠራል።
እነዚህ ነፋሳት ከምድራችን ውጫዊ ከባቢ አየር እና የመግነጢሳዊ መስክ (Magnetic field) ጋር ሰበቃ (friction) በሚፈጥሩበት ጊዜ ሰማዩ ላይ የተለያየ ህብረቀለማት ያላቸው ነፋሳት ሲነፍሱ ሰማዩ ላይ አውሮራ (Aurora) ተከሰተ ይባላል።
አውሮራ በሰሜናዊው እና ደቡባዊው ዋልታ ላይ ብቻ አልፎ አልፎ የሚከሰት የሰማይ ላይ ትንግርት ሲሆን ከምድር የከባቢ አየር ጋዞችም ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።
እነዚህ ጋዞች በዋነኝነት ናይትሮጅን እና ኦክስጅን ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ ሌሎች የጋዝ አይነቶችም ይካተታሉ።
የአውሮራን ቀለም የሚወስነው ፕላስማ፣ ሰበቃ የፈጠረበት የከባቢ አየር ጋዝ እና ሰበቃው የተፈጠረበት ቦታ ከምድር ወለል ያለው ከፍታ ትልቅ ነው።
ፕላስማው ሰበቃ የፈጠረው ከምድር ወለል እስከ 96 ኪ.ሜ ርቆ ከሚገኝ የናይትሮጅን ጋዝ ጋር ከሆነ አውሮራው ሰማያዊ ቀለም ይኖረዋል።
ፕላስማው ከ96ኪ.ሜ በላይ ርቆ ከሚገኝ የናይትሮጅን ጋዝ ጋር ሰበቃ ከፈጠረ አውሮራው ወይነጠጅ ቀለም በውስጡ ይይዛል።
ፕላስማው ከምድራችን ወለል ከ 96ኪ.ሜ እስከ 241ኪ.ሜ ርቆ ከሚገኝ የኦክስጅን ጋዝ ጋር መስተጋብር ከፈጠረ አውሮራው አረንጓዴ ቀለም ይይዛል።
ፕላስማው መስተጋብር የፈጠረው ከምድር ወለል ከ241ኪ.ሜ በላይ ከሚገኝ የኦክስጅን ጋዝ ጋር ከሆነ አውሮራው ቀይ ቀለም በውስጡ ይይዛል።
ከላይ እንደተጠቀሰው አውሮራዎች በሁለት አይነት መልኩ ሊከሰቱ ይችላሉ። አንደኛው በሰሜናዊው ዋልታ ብቻ የሚታየው አውሮራ ቦሪያሊስ (Aurora Borealis) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በደቡባዊው ዋልታ ላይ ብቻ የሚታየው አውሮራ አውስትራሊስ (Aurora Australis) የሚባለው ነው።
አውሮራዎች ጠንካራ በሚሆኑበት ጊዜ የራዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና የስልክ ሞገዶችን በማወክ ሊያስተጓጉሉ እንደሚችሉ የዋይልስዊድን ዘገባ ያመለክታል።