"የገቢና የወጪ ንግድ ላይ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ መፈቀዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ያሻሽለዋል"-የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አረጋ ሹመቴ (ዶ/ር) *************"መመሪያው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከባለቤትነት ድርሻ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል"-የሕግ ባለሙያ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ

9 Days Ago
"የገቢና የወጪ ንግድ ላይ  የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ መፈቀዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ያሻሽለዋል"-የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አረጋ ሹመቴ (ዶ/ር)    *************"መመሪያው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከባለቤትነት ድርሻ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል"-የሕግ ባለሙያ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ

የውጭ ባለሀብቶች ከማዳበሪያ እና ነዳጅ በስተቀር በሁሉም የገቢና ወጪ ንግድ ላይ በጅምላ እና በችርቻሮ እንዲሳተፉ ተፈቅዷል፡፡

ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት ታሪኳ የውጭ ኢንቨስተሮችን በተወሰኑ የስራ ዘርፍ ብቻ እንዲሰሩ ፍቃድ ትሰጥ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በዚህም  ከዓለም ብሎም ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ኢኮኖሚዋ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ነው ማለት የሚያስችል ቢሆንም፤ የተወሰኑ የሚባሉ ማሻሻያዎች ሲደረጉም ነበር፡፡

ከ2002 ዓ.ም በፊት የነበረው የኢንቨስትመንት ደንብ የውጭ ኩባንያዎች ሊሠሩበት የሚችሉትን ዘርፍ የሚጠቅስ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ በተሻሻለው ደንብ የቢዝነስ ሀሳቦችን በመዘርዘር ከተጠቀሱት ውጪ ባሉት መስኮች የመሰማራት መብትን የሚሰጥ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ይህን አካሄድ በምትከተልበት በአሁኑ ወቅት፤ የውጭ ኩባንያዎች በገቢ እና ወጪ እንዲሁም በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ በማድረግ መመሪያው መውጣቱን ይፋ አድርጋለች፡፡

ይህም ለኢትዮጵያውያን ብቻ ይፈቀዱ የነበሩ ዘርፎች ላይ የውጪ ባለሀብቶችን በማሳተፍ እና ገበያውን ክፍት በማድረግ የሀገሪቱ የግብይት ሥርዓትን በማስተካከል በወጪ ንግድ ዘርፍ ያላትን ተወዳዳሪነት ይጨምራል የሚል ግምት ተሰጥቶታል፡፡

 በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አረጋ ሹመቴ፤ ይህንን ለውጥ በማድረግ የውጭ ኩባንያዎች በመንግስት ተይዘው ከነበሩ የአገልግሎት መስጠት ጀምሮ ወደ ንግዱ መስክ እንዲገቡ መፈቀዱ  የራሱ ጠቀሜታም ጉዳትም አለው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር በዋናነት የውጭ ባለሀብቶች በአምራች ዘርፍ፣ በግንባታ እና በሰፋፊ እርሻ ላይ እንዲሁም በሆቴል ዘርፍ ብዙም በማይባል ደረጃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸው እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡

አቶ አረጋ በገበያው ከፍተኛ አቅርቦት እንዲኖር በማስቻል እና ያለውን የዋጋ ግሽበት በማረጋጋት  ዘመናዊነትን የተላበሰ ግብይት እንዲፈጠር ያስችላል ሲሉ ያለውን ጠቀሜታ ይገልፃሉ፡፡

አቅርቦት እና ፍላጎት ሲዘውሩት የነበረን ኢኮኖሚ፤ በሳይንስ የተመራ እና በሚኖረው በቂ አቅርቦት ሳቢያ በመሀል የሚገቡ ጣልቃ ገቦች እንዲወገዱ ያስችለዋል ይላሉ፡፡

የውጭ ኩባንያዎች እንደተጠበቀው ከንግዱ ወደ ማምረት ሂደት ብሎም የሚያገኙትን ገቢ እና ካፒታል እዚሁ ፈሰስ ማድረግ እና ኢኮኖሚውን ማገዝ ካልቻሉ ፤ በተለይም  ያላቸውን ምርት ብቻ አምጥቶ መሸጥ ላይ  ካተኮሩ የምርት ማራገፊያ ከመሆን ባሻገር  የዶላር እጥረቱን አሁን ካለበት ሊያብሰው እንደሚችልም ነው የሚገልፁት፡፡

የውጭ ምንዛሬ፣ የስራ ዕድል፣ የልምድ ልውውጥ ፣ ዘመናዊነት ይዟቸው የሚመጣው መልካም ነገሮች እንደሚሆኑም ይጠበቃል ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ አረጋ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል፤ የገቢ እና የወጪ ንግድ ከነችግሩ ለሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ብቻ ቢተው መልካም ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ናቸው፡፡

የገንዘባችን የመግዛት አቅሙ ከዶላር አንጻር ዝቅተኛ በመሆኑ መመሪያው ለውጭ ባለሀብቶች በጥቂት ገንዘብ ባለቤት የመሆን እድል የሚሰጣቸው ሲሆን፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከገበያው እንዲወጡ በማድረግ የተቀጣሪነት ሚና ያላብሳል ሲሉ ይተቻሉ፡፡

ይህም የንግዱ ዘርፍ በውጪ ባለሀብቶች ቁጥጥር ስር እንዲውል ያደርገዋል በማለት ለአብነት ኬኒያን እና ደቡብ አፍሪካን ይጠቅሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በእንቅስቃሴ ላይ እንደመገኘቷ እና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ፈራሚ በመሆኗ በቀጠናው የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራት በሯን ለዓለም የንግድ ስርዓት ክፍት ማድረጓ አስፈላጊ ቢሆንም፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማዳከሙ ቸል ሊባል የሚገባው ሀሳብ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት፤ መመሪያው የተሻለ ልምድ፣ ዕውቀት፣ የገዘፈ ካፒታል፣ የቴክኖሎጂ አግባቦት እንዲሁም የተለያዩ ሀገራትን ልምድ የቀሰሙ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገራችን እንዲመጡ ይጋብዛል ይላሉ፡፡

ሆኖም ግን የንግድ ስርዓቱ ብዙም ባላደገ ፣ ባልዘመነ እና በዕውቀት ያልተደገፈ በሆነበት ግብይት ውስጥ የቆዩትን የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች የመወዳደር አቅማቸውን እንዲያጡ ብሎም ከገበያው እንዲወጡ ያደርጋል የሚል ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

የውጭ ባለሀብቶቹ የመጡበት ዳራ የተጠናከረ እና የዘመነ በመሆኑ  መመሪያው ተግባራዊ ሲሆን የመንግስት የመቆጣጠር አቅምን ይፈተናል ያሉ ሲሆን፤ ትክክለኛ ግብር ከፋይ እንዲሆኑ በማድረግ  ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን መቅረፅ እንደሚያስልግም ጠቅሰዋል፡፡  

የንግድ ባለቤትነት የብዙ ነፀብራቅ ውጤት ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ ሴክተሩ በኢትዮጵያውን ብቻ ቢያዝ መልካም መሆኑን ይናገራሉ።

በአፎሚያ ክበበው

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top