የከሰል ጭስ በጥንቃቄ ካልተያዘ ሕይወትን ሊያሳጣ እንደሚችል ያውቃሉ?

7 Mons Ago 2297
የከሰል ጭስ በጥንቃቄ ካልተያዘ ሕይወትን ሊያሳጣ እንደሚችል ያውቃሉ?

በአሁኑ ወቅት ካለው የአየር ፀባይ ጋር ተያይዞ አልያም ቅዝቃዜን ለመከላከል በሚል እና ለምግብ ማብሰያነትም ጭምር ሰዎች ከሰልን በብዛት ይጠቀማሉ::

ይሁንና ከሰል በአግባቡና በጥንቃቄ ካልተያዘ ሕይወትን ከማሳጣት እስከ የዕድሜ ልክ ህመም እንደሚዳርግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ለምግብ ማብሰያነት እና ቅዝቃዜን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውለውን ከሰል ስንጠቀም ከጭሱ የሚወጣውን መርዛማ ጋዝ እንዴት መከላከል እና ጉዳት በማያመጣ መልኩ መጠቀም ይቻላል?   

ከሰልን ሲጠቀሙ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካላደረጉ የከሰል ጭስ ሞትን ጨምሮ የዕድሜ ልክ ህመም ለሆኑት የአዕምሮ ጉዳትና የልብ በሽታ ያጋልጣል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ የከሰል ጭስ በዓይን የማይታይና ሽታ አልባ መርዛማ ጋዝ አለው፡፡ 

ይህ ጋዝ የሚፈጠረውም ጋዝ፣ ዘይት፣ ከሰል ወይም እንጨት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው ባለማለቃቸው ነው፡፡ 

የከሰል ጭስ በአካባቢያችን በሚኖርበት ጊዜ አየር ወደ ውስጡ በሚሳብበት ጊዜ፤ በደም  ውስጥ በመግባት የቀይ የደም ህዋስ አካል የሆነውና ኦክስጅን ተሸክሞ ለተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ከሚያደርሰው ሂሞግሎቢን ጋር በመቀላቀል ካርበ ኦክሲሄሞግሎቢን ይሆናል፡፡

ይህ ከሆነ በኋላ ደም ኦክስጅን መሸከሙን ያቆማል፤ በዚህ የተነሳ የህዋሶቹ አነስተኛ ክፍሎች ይጎዳሉ፤ ብሎም ይሞታሉ፡፡ 

በከሰል ጭስ ወይም በካርበን ሞኖክሳይድ የተጠቃ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች፤ የራስ ምታት፣ ራስ ማዞርና መታመም፣ የድካም ስሜትና ግራ መጋባት፣ ሚዛንን ለመጠበቅ መቸገር፣ የዕይታና የትውስታ ማጣት፣ ራስን መሳት፣ በአንድ ነገር ላይ አትኩሮት ማጣት፣ የሆድ ሕመም እንዲሁም ለመተንፈስ መቸገር ምልክቶች ሊታዩበት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

የከሰል ጭስን እንዴት መከላከል ይቻላል፤

በከሰል ምግብ ማብሰል ሲያስፈልግ በቂ አየር እንዲያገኝ (ከተቻለ ከቤት ውጭ) ከቤት ውጭ ማብሰል ካልተቻለ ደግሞ ሙሉ በመሉ ከተቀጣጠለና ጭሱ መጥፋቱ ሲረጋገጥ ወደ ቤት ማስገባት ይመከራል፡፡

በተጨማሪም የከሰል ምድጃ እየተጠቀሙ በር እና መስኮት አለመዝጋት፣ በከሰል ምግብ አብስለው ሲጨርሱ በውኃ ማጥፋትና በርና መስኮት በመክፈት ቤቱን ማናፈስ እንዲሁም ከሰል ቤት ውስጥ አለማቀጣጠልን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ከዚህ ባለፈም ከሰል ቤት ውስጥ አቀጣጥሎ ማሸለብ ወይም መተኛት አደጋው የከፋ በመሆኑ ከእነዚህ ድርጊቶች መቆጠብ እንደሚያስፈልግ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top